ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ወደ እውቀት መር-ኢኮኖሚ ለማሻገር ለትምህርት ምርምርና ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 06/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ወደ እውቀት መር-ኢኮኖሚ ለማሻገር ለትምህርት ምርምርና ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከሃምሌ 5 እስክ ሃምሌ 8 2013 ዓ.ም ለ4 ቀናት የሚቆይ ''ወደ እውቀት-መር ኢኮኖሚ'' በሚል መሪ ሃሳብ የትምህርት፣ የመርምር፣ የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን ትላንት ተከፍቷል።

በመድረኩ የከፍተኛ ትምሀረት የስራ ሃላፊዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ፣ የኢንዱስትሪ ባለሃብቶች የመንግሰት ፖሊሲ አውጪዎችና የምርምር ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ልማት በሚል ርዕስ የዓለም አቀፍና የአህጉር አቀፍ ተሞክሮዎችና እይታዎች በዛሬው መድረክ ተዳሰዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የ10 አመት የልማት መሪ እቅድ ከ2063 የአፍሪካ የልማት ግቦች ጋር የተናበቡ ስለመሆናቸው ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አገሪቷን ወደሚፈለገው የእደገት ደረጃ ለመውሰድ በእውቀት የሚመራ ኢኮኖሚን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ እውቀት-መር  ኢኮኖሚ ለማሻገር ለትምህርት፣ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

አገሪቷ ላይ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣  እውቀትን የሚያደራጁ፣ እውቀትን የሚያሻግሩና የሚመሩ በዘርፉ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

''ኢትዮጵያ እንደ አገር ማደግ አለባት የህዝቦቿ ኑሮ ሊቀየር ይገባል'' ያሉት ሚኒስትር ዴታው ለዚህም በትስስር ለመስራት ስምምነት ላይ የተደረሰ እንደሆነ ገልጸዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉም ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የአገሪቷን ቀጣይ የልማት እድገት ጉዞ እንዲደግፍ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በእውቀት የሚመራ ኢኮኖሚን ለመመስረት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በእውቀት የሚመራ የኢኮኖሚ ሽግግርን እውን ለማድረግ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን አደራ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አገሪቷ በዲፕሎማሲና በሰላም ዘርፍ ምን ምን ተግባራትን እያከናወነች እንደሆነችም በመድረኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ገለጻ ተደርጓል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩንና አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ለተሳታፊዎቹ  ገለጻ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም