ቀጥታ፡

በሲዳማ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ

ሀዋሳ ሐምሌ 6/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል " በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያን እናልብሳት " መሪ ሀሳብ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

በታቦር ተራራ አረንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፍና የአረጋውያን የቤት እድሳትን በሀዋሳ  ሶስት ክፍለ ከተሞች በመገኘት አገልግሎቱን ያስጀመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ናቸው።

አቶ ደስታ በወቅቱ እንዳሉት ፤ የሲዳማ ህዝብ እራሱን  በራሱ ለማስተዳደር  ባመነበትና  በታገለበት አውድ ሁሉ ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለክልሉ ህዝብ አስፈላጊ የሆኑ የልማት  ስራዎችን በስፋት  እያከናወንን  እንገኛለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ይህንን ስራ ለማስቀጠል የወጣቶች ተሳትፎ በእጅጉ  እንደሚያስፈልግ  አስታወቀዋል።

በተለይ "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚለው ፕሮግራም በክልሉ 300  ሚሊዮን ችግኝ  ለመትከል ታቀዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ጠቅሰው፤ ለዚህ ስኬት ወጣቶች ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በክረምቱ አካባቢያችንን ከማልበስ ባለፈ  የአቅመ ዳካሞችን ቤት  በማደስና  ለተጎዱ  ወገኖች ደም በመለገስ አሌኝታነታችሁን ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል ያሉት አቶ ደስታ፤   በእንቅስቃሴያቸው የክልሉ መንግስት ከጎናቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ መሰማራታቸው ለህብረተሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባለፈ የአዕምሮ እርካታ በማጎናጸፍ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም  ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት  ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ያከናወኑት ስራ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትም አውስተዋል።

የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ  አለሙ  በበኩላቸው ፤ ዘንድሮ  በሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ 540 ሺህ ወጣቶች እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል።

እስከ መስከረም 30/ 2014 ዓ.ም. በሚዘልቀው የበጎ ፈቃድ  አገልግሎትም  ወጣቶቹ በ13  ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በዚሁ እንቅስቃሴም ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት የልማት አስተዋጽኦ   እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ከተገኙት መካከል የሀዋሳ ከተማ ወጣት ምንተስኖት መኩሪያ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ሳይማር ያስተማርኝን ማህበረሰብ ዛሬ በጉልበቴና በእውቀቴ ለመካስ በመቻሌ  ደስታ ተሰምቶኛል ብሏል።

የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ወጣት በረከት ተስፋዬ በበኩሏ፤ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት  በመሳተፍ ህብረተሰቡን ለማገልገል በስራው  እየተሳተፈች መሆኗን ገልጻለች።

ዛሬ በተጀመረው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ላይ  ከክልሉ ወረዳዎችና  ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም