በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት እየለወጡት መሆኑን የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት እየለወጡት መሆኑን የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎች ተናገሩ
ሐረር ሐምሌ 6 /2013 (ኢዜአ) በየዓመቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እየተተከሉ ያሉ የዛፍ ችግኞች አካባቢያቸውን ወደ አረንጓዴነት እየለወጡ መሆናቸውን በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በዞኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ማኖር መርሃ ግብር ዛሬ ሲጀመር በዕለቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በመሳተፍ ከ37 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ተገልጿል።
በዞኑ ሜታ ወረዳ በከልቻ ኦሮሚያ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ መሰረት ከበደ እየጨመረ የመጣውን በረሃማነት ለመከላከል የምትክለውን ችግኝ እንደ ልጄ ተንከባክቤ አጸድቀዋለሁ ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በቀበሌው ተፋሰስ ላይ የተከሏቸው የዛፍ ችግኞች በረሃማነትን በመከላከል አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት እንደቀየረውም ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳት እየተመለሱ መሆናቸውንና በበጋ ወራት የሚያጋጥመው የዝናብ እጥረት እየተስተካከለ በመምጣቱ ሰብል በማልማት መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
በተፋሰሶች ላይ በተከታታይ ዓመታት የተተከሉ የዛፍ ችግኞች ባስገኙት ለውጥ የቀበሌው ነዋሪዎች በብዛት በመውጣት ችግኝ የመትከል ልምዱ እያዳበሩ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር መሐመድ ኡስማን ናቸው።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉትን ችግኞችን ተንከባክበው ለማሳደግ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራን እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተከናወነበትና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት እየተከናወነ ባለበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ ማኖር መረሃ ግብር በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከ265 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ስራው መጀመሩን ተናገረዋል።
ዛሬ በዞኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ከ37 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደተከሉም አስታውቀዋል።
የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ ሕዝቡ በፈቃደኝነት በብዛት በመውጣት አሻራውን እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የሚከናወነው በዞኑ 20 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 315 ተፋሰሶች ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች 85 በመቶው መጽደቃቸውም ተመልክቷል።