ቀጥታ፡

የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ኢትዮጵያ ግድቡን ለተለያዩ አገራት ለማስረዳት እድል ፈጥሯል ሲሉ አንድ ምሁር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ሀምሌ 6/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጸጥታው ምክር ቤት መታየቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለተለያዩ አገራት ለማስረዳት እድል ፈጥሮላታል ሲሉ የአዲስ አበባ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ማዕከል መምህር ሣሙኤል ተፈራ ተናገሩ።

ባሳለፍነው ሐሙስ በሱዳን ጥያቄ አቅራቢነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ መወያየቱ ይታወሳል።

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ግድቡ በአፍሪካ ኀብረት አሸማጋይነት በሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ዳግም እንዲታይ ጉዳዩን መርቶታል።

ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔም ጉዳዩ 'ከምክር ቤቱ ኃላፊነት ውጭ' ስለሆነ ተጠባቂ መሆኑን ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሣሙኤል ተፈራ የሚናገሩት።

ከዚህ ቀደምም በግብጽና በሱዳን አማካይነት የግድቡ ጉዳይ በምክር ቤቱ እንዲታይ ያቀረቡትን ጥያቄ ምክር ቤቱ ጉዳዩ እንደማይመለከተው በመግለጽ ለአፍሪካ ኅብረት መላኩን አስታውሰዋል።

ይህም ሆኖ ግድቡ በመንግስታቱ ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት ለውይይት መቅረቡ ግብጽና ሱዳን ካሰቡት በተቃራኒው ኢትዮጵያ ጉዳዩን በበለጠ ለተለያዩ አባል አገራት እንድታስረዳ እድል ሰጥቷታል ብለዋል።

ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት መላኩ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸው ሦስቱን አገራት በቅርበት የሚያውቃቸው ኅብረቱ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት መሥራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

ግብጽና ሱዳን በጉዳዩ ላይ ለመግባባት ቁርጠኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው አሁን በአፍሪካ ኅብረት ከሚካሄደው ድርድር ውጭ ሌሎች አማራጮችን እያፈላለጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ዘላቂ መፍትሔ አያስገኝም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሣሙኤል ኢትዮጵያ ግን መፍትሔ ስለምትሻ በግድቡ ላይ የማይለዋወጥ አቋሟን አሁንም ማጠናከር ይገባታል ነው ያሉት።  

በሌላ በኩል በአንዳንድ አገራትና አረብ ሊግ ውሃውን የአረብ የደህንነት ጉዳይ ማድረግና  አረባዊ ማንነት ለማላበስ የሚደረገው ሙከራ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን የፖለቲካ ተቋም በተመለከተ የምታራምደው ዲፕሎማሲ በቅጡ ማጤንና የአረብ ሊግና  የአረብ ህዝብን የለየ አቋም ሊኖር እንደሚገባ ነው ምክረ-ሐሳብ የሰጡት።   

"የግብጽ ፍላጎቷ በአጭሩ ስትጠቀልለው እኛ እንዳናድግ ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሣሙኤል ግድቡን በተመለከተ የሚካሄደው የዲፕሎማሲ ሥራ ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቹ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በመጨበጥ በግድቡ ላይ ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ግድቡን በተመለከተ የሚሰሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ የሚችለውን ተጽዕኖ ፈጣሪ የዲፕሎማሲ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።     

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መሙላት መጀመሯ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም