ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር ሰነዶችን በኦንላይን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር ሰነዶችን በኦንላይን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ የውክልና ሰነዶችን በአጭር ጊዜ በኦንላይን ለማረጋገጥ፣ በሀሰተኛ ሰነዶች ሊፈፀም የሚችልን ማጭበርበር ለማስቀረትና ወንጀልን ለመከላከል ይረዳል ተብሏል፡፡

ደንበኞች ሰነዶችን ለማረጋገጥ የሚደርስባቸውን መጉላላት በመቀነስ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ በስምምነቱ በመታገዝ ከዚህ በፊት በኤጀንሲው የተመዘገቡና የተረጋገጡ ሰነዶችን ለመጠቀም ያስችለዋልም ተብሏል፡፡

በባንኩ የማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ ባንኩ ባሉት 1 ሺህ 700 ቅርንጫፎች መረጃዎችን በመለዋወጥ ለደንበኞች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሰነዶችና ፎቶዎች ህጋዊ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ በማረጋገጥ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ከኤጀንሲው የሚያገኘውን የደንበኞች የውክልና ሰነድ በባንኩ ከሚገኘው ሰነድ ጋር በማመሳከር አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚያስችለውም ገልፀዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በበኩላቸው አሰራሩ ኤጀንሲው የመረጃ አያያዙን በማዘመን የሰነዶችን ትክክለኛነትና ህጋዊነትን በአጭር ጊዜ እንዲያረጋግጥ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ተግባራዊ ሲደረግ ደንበኞች ሰነዶችን ለማረጋገጥ የሚወስድባቸውን ከሰባት እስከ አስር ቀናት የሚፈጅ ጊዜ ማስቀረት እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው ከ25 በላይ አዳዲስ ቴክኖለጂዎችን በማበልፀግ ሀሰተኛ ሰነዶች የማጋለጥ ስራ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም