ቀጥታ፡

የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አቅምን ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ ሐምሌ 6/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ዕሴት በመጨመር ለገበያዎች የሚያቀርቡ የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አቅም ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ከሌሎች የዘርፉ ቡድን አባላት ጋር የይርጋለም  የተቀናጀ  የግብርና ምርቶች  ማቀነባበሪያ ፓርክን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

አምባሳደር ግርማ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሚከናወነው የግብርና ሥራ አርሶ አደሩንና የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ አድጎ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ዘርፉን  ማዘመንና ውጤታማ አሰራር መከተል ወሳኝ ነው፡፡

በተለይ የግብርና ጥሬ ዕቃዎች በማቀነባበር እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የጀመሩ ፋብሪካዎችን አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሃብቶችን ለመሳብ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ሆኖ እንዳገኙትም  አማካሪው ተናግረዋል፡፡

ወደ ሥራ የገቡ ፋብሪካዎችም ሆኑ ፍላጎት  ያላቸው የሀገር ውስጥና  የውጭ  ባለሃብቶች  የሚያነሷቸውን የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና መቆራረጥ፣ የበጀትና የግብአት አቅርቦት  ችግሮች መፍታት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ከኤሌክትሪክ ሃይል   ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የብድር አቅርቦት ለማሟላት ከባንኮች  ጋር  በመነጋገር ላይ  ይገኛል  ብለዋል፡፡

የግብአት አቅርቦት ለማሻሻል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉባቸው አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበቂ ሁኔታ እንዲያመርቱ የማስተባበርና ትስስር እንዲፈጥሩ ለማስቻል ትኩረት መሰጠቱን አምባሳደር ግርማ አስረድተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተደድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ አቅም  ለመጠቀም  በተሰጠው ትኩረት 11 ፋብሪካዎች ወደሥራ በመግባት ላይ  እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ  አስተማማኝ ሰላም  የሰፈነበት  የሥራ  አካባቢ በመፍጠር :የባንክና የጉምሩክ  አገልግሎቶች የማደራጀት  ስራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን ም ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች በህብረት ሥራ ማህበራት በማደራጀት ከፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በቀጥታ ምርታቸውን የሚያቀርቡበት አሰራር  ወጥነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ መዘርጋቱንም አቶ ደስታ አስረድተዋል፡፡

የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋሪካዎች ወደምርት ሂደት መግባት በለፋው ልክ ጥቅም ሳያገኝ ለኖረው አርሶ አደር የድል ዜና ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ለአርሶ አደሩ ምርት የሚያሳድጉ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም  ተናግረዋል፡፡

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ  እንዲገባ የሚያስፈልጉ ተቋማት መደራጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብሩ ወልዴ ናቸው።

ዋና ሥ አስፈጻሚው እንዳመለከቱት፤ በፓርኩ እስካሁን ሁለት የአቦካዶ  ዘይት  የሚያመርቱ ፣ አራት ቡናና ወተት አምራች ፋብሪካዎች  ሥራ ጀምረዋል፡፡

ከፋብሪካዎች ጋር በተፈጠረው ትስስርም ከ90 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ከ4 ሺህ 200 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ማግኘታቸውን አቶ ብሩ አስታውቀዋል፡፡

በፓርኩ ቡና በማቀነባበር ለዓለም ገበያ  ለማቅረብ ከ140 ሚሊዮን  ብር በላይ  ወጪ  የተቋቋመውና የፋብሪካ ግብአቶች እያስገባ ያለው "ሄብሮን" የኢትዮጵያ ቡና አምራች የግል ማህበር አንዱ ነው፡፡

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮሚዮ ዛራሜላ ቡና በማቀነባበርና በመቀመም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች ለማቅረብ የፋብሪካ ተከላና የምርት አቅርቦት ለማቀላጠፍ አርሶ አደሮች ባመረቱት ልክ ለመረከብ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ትስስር እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፓርኩ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ፋብሪካ እየተከለ  ያለው የ"ዋይ ቢ ኤም "  የአቦካዶ  ዘይት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ጸጋአብ መለሰ እንዳሉት፤ ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ በቀን ከ80 ቶን በላይ አቦካዶ የመፍጨት አቅም አለው፡፡

ለዚህም ከ70 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በ14 የህብረት ሥራ ማህበራት በማደራጀት የጥሬ ምርት አቅርቦት ትስስር መፍጠራቸውን አመልክተው፤ ከ780 ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻሉ የአቦካዶ ዝርያዎች ለመሸፈን እየሰራን ነው  ብለዋል፡፡

ምርትን የሚጨምሩና ጊዜን የሚቆጥቡ የተሻሻሉ የአቦካዶ ዝርያዎች ከውጭ በማስመጣት ለአርሶ አደሩ  እንደሚያሰራጩም ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ከ450 በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ  ሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና   በአንድ ወር ውስጥ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት  እንደሚገባ   ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ በ294 ሄክታር መሬት  ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም