በቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ለሙገር ሲሚንቶ የፎርፌ ውጤት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ለሙገር ሲሚንቶ የፎርፌ ውጤት ተሰጥቷል
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሙገር ሲሚንቶ የፎርፌ ውጤት አግኝቷል። ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያና ሙገር ሲሚንቶ ያደረጉት የ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ የቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሳይጠናቀቅ መቋረጡ ይታወሳል። ለመቋረጡ ምክንያት ሆኗን የተባለው "ዳኞች ባሳለፉት ውሳኔ ደስተኛ ያልነበሩት የፌዴራል ማረሚያ አሰልጣኝ ቡድናቸው ጨዋታውን አቋርጦ እንዲወጡ በማድረጋቸው" መሆኑን ተገልጾ ነበር። የጨዋታው ኮሚሽነር ባቀረቡት ሪፖርት አማካኝነት የውድድርና ስነስርአት ኮሚቴ የፌዴራል ማረሚያ ቡድን ጨዋታውን ማቋረጡ አግባብነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ፤ ሙገር ሲሚንቶ የፎርፌ ውጤት እንዲያገኝ መደረጉን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ትናንት ኮሚቴው ተሰብስቦ ባሳለፈው ውሳኔው መሰረት ሙገር ሲሚንቶ የሶስት ለባዶ ውጤትና ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል። በተጨማሪም በቀረበው ሪፖርት ውስጥ የፌዴራል ማረሚያ አሰልጣኝንና የቡድን መሪውነ ለመቅጣትና ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ የውድድርና ስነስርአት ኮሚቴ ተጨማሪ ማስረጃዎች የታከለበት ሪፖርት ድጋሚ ኮሚሽነሩ እንዲያቀርብ መግለጹን አክለዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የሶስት ጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ተጠናቀው አራተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙገር 20 ለ 12 እየመራ ጨዋታው መቋረጡንና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታውን ሁለት ለአንድ እየመራ እንደነበር አስታውሰዋል።