በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል... ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል... ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2013(ኢዜአ) በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል በማለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።
ሊጀመር አስር ቀናት በቀረው የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ ውሃ ዋና እና በብስክሌት ትሳተፋለች።
በአትሌቲክስ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን በመወዳደር ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገልፃለች።
በውድድሩ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ውጤት ለማምጣት አትሌቶች ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑም ተናግራለች።
የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሲታሰብ አበበ በቂላ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያውን ለሀገሩ ያመጣበት ስፍራ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም ያለው ነው፤ እኛም ለዚህ ውድድር ትልቅ እንግዶች ነን ብላለች።
በዚህ ታሪካዊ ቦታ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችም ይህንኑ ክብር የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት ማድርጋቸውን ኮማንደር ደራርቱ ገልፃለች።
አትሌቶቹ በኮቪድ ምክንያት ከኦሎምፒኩ እንዳይሰረዙ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።
የቡድኑ የአሰልጣኞች አስተባባሪና የ10 እና 5 ሺህ ሜትር ዋና አሰልጣኝና ኮማንደር ሁሴን ሽቦ በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በኦሎምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች ከሌሎች ዓመታት በተለየ ለስምንት ወራት ሆቴል በመግባት ልምምድ ሲያደረጉ መቆያታቸውን አስታወሰው፣ ይህም ጥሩ ውጤት ለማምጣት የተሻለ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በማራቶን ኢትዮጵያን የምትወክለው አትሌት ሮዛ ደረጀ እና በ3 ሺህ መሰናክል የሚወዳደረው አትሌት ሃይለማሪያም አማረ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ኦሎምፒክ የሚካፈሉ አትሌቶችና የልዑካን ቡድን አባለት ዛሬ ምሽት በብሄራዊ ቤተመንግስት ሽኝት እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል።