ቀጥታ፡

የሶስትዮሽ ድርድሩ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት እንዲቋጭ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሰራለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት እንዲቋጭ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የድርድሩን ሂደት አስመልክቶ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ በመርህ ስምምነቱ መሰረት ድርድሩ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሷል።

ድርድሩ በተለያየ ምክንያትና ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዝ ጥረት በሚያደርጉ አካላት ሲጓተት መቆየቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ኢትዮጵያ ግልጽ አቋሟን አስቀምጣ የድርድር ሂደቱ በፍጥነት እንዲቋጭ ጥረት ማድረጓን ገልጿል።

ነገር ግን ጉዳዩን ጭራሽ ወደማይመለከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጸጥታ ምክር ቤት እስከመውሰድ መደረሱ ተገቢ እንዳለነበረ አመላክቷል።

በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የሚካሄደው የድርድር ሂደት የሁሉንም ወገን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ ውጤት እንደሚያመጣ እምነቱን ገልጿል።

እስካሁንም ድረስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱ እንደሚታወቅ ጠቅሷል።

ድርድሩ የቆዩ ችግሮችን መፍታት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፤ “የሶስትዮሽ ድርድሩ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት እንዲቋጭ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሰራለች” ሲል አረጋግጧል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሚያቀርቡት ሃሳብ መሰረት ኢትዮጵያ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን አመልክቶ፤ ሱዳንና ግብጽም ሂደቱ ፍሬ እንዲያፈራ በትብብር እንዲሰሩ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም