ለፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ሊለማለት ነው… የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

65

ሐምሌ 6/2013(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) ሊያለማለት መሆኑን አስታወቀ።

የመረጃ አስተዳደሩ የስፖርት ቡድኑ መረጃ ለደጋፊዎቹና ለማህበርሰቡ ባሉበት ለማድረስ የሚያስችል ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) ከፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ስራ አስኪያጅና የቦርድ አመራሮች ጋር ቡድኑን የዲጂታል ፖርታል ባለቤት ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደሩ ከፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሊንክድኢን ከመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ከቴሌ ብር ጋር በማገናኘት አገልግሎት መስጠት የሚያስችልም ነው ተብሏል።

የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር በአንድ ወር ጊዜ አልምተው እንደሚያሰረክቡ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ጉዞ ወደ ሁሉም ዘርፎች ለማውረድ እንሰራለንም ብለዋል።

የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ ባለሙያዎችን በማሟላት የመረጃ አስተዳደሩ ሳይቆራረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ የክለቡን ታሪክ፣ ዕለታዊ የእንቅስቃሴ መረጃ፣ የገቢ ማስገኛ ሽያጭ፣ የደጋፊዎች መረጃ፣ ድጋፍ ማሰባሰቢያና የመሳሰሉትን መረጃዎች አስተሳስሮ የሚያዝ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም