በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጎርፍ መከላከል ሥራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጎርፍ መከላከል ሥራ እየተካሄደ ነው
ጎንደር ፤ ሐምሌ 5/2013(ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በክረምት ወራት በጣና ሐይቅ ገባር ወንዞች የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጎርፍ መከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ጣና ሐይቅ ሞልቶ በመፍሰሱ የተፈናቀሉ ከ29ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውም ተመላክቷል።
በዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ አረጋልኝ አዳነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጣና ሐይቅ አዋሳኝ በሆኑት ምዕራብና ምስራቅ ደምቢያ ወረዳዎች "ድርማ" በተባለ ወንዝ ላይ የጎርፍ መከላከያ ግድብ እየተሰራ ነው፡፡
የጎርፍ መከላከያ ግድብ ሥራው የክልሉ መንግስት በመደበው 700ሺህ ብር ወጪ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እስካሁንም በወንዙ ግራና ቀኝ ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የጎርፍ መከላከያ የአፈር ግድብ መሰራቱን ባለሙያው አስረድተዋል።
በመንግስት ከሚከናወነው በተጨማሪ የሁለቱ ወረዳ ነዋሪዎች ውሃው ሰብሮ የሚወጣባቸውን አካባቢዎች በመለየት በአፈር በተሞሉ ጆንያዎች የወንዙን ግራና ቀኝ እየዘጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የጎርፍ አደጋ ቢከሰት እንኳ ነዋሪዎችን በፍጥነት ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ማንቀሳቀስ እንዲቻል በወረዳዎቹ ሁለት ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን ለማቋቋም በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ ለመጠለያዎቹ የሚያስፈልጉ ድንኳኖች፣ የዕለት ምግብና መድሃኒቶችን ጭምር ከውዲሁ ለማሟላት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
"ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅት የጣና ሐይቅ ሞልቶ በመፍሰስ ከቄያቸው የተፈናቀሉ 29 ሺህ አባወራና ቤተሰቦቻቸው ወደ መኖሪያ ቄያቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አቶ አረጋልኝ አመልክተዋል።
አርሶ አደሮቹ በዘንድሮ ክረምት ለእርሻ ሥራ የሚጠቀሙበት የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅትም ለሁለተኛ ጊዜ 5ሺህ ኩንታል የቀለብ እህል ድጋፍ እየተጓጓዘላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በወቅቱ ከቤት ንብረታቸው ቢፈናቀሉም መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸው መቃለሉን የገለጹት ደግሞ በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የሮቢት ቀበሌ አርሶ አደር በየነ ሞገስ ናቸው፡፡
ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ሰጠኝ መኳንንት በበኩላቸው፤ ክረምት በመጣ ቁጥር የ"ድርማ" ወንዝ የጎርፍ አደጋ እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
ዘንድሮ ችግሩ እንዳይከሰት መንግስት ለጀመረው የጎርፍ መከላከል ሥራ በጉልበታቸው ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡