ቀጥታ፡

የልማትና እድገት ግቦችን ለማሳካት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ማጠናከር ይገባል-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ ሀምሌ 5/2013(ኢዜአ) አገራዊ የልማትና የእድገት ግቦችን ለማሳካት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የመጀመሪያው የትምህርት ምርምር፣ የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ትስስር ጉባኤ በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት ነው፡፡


መድረኩ "ወደ እውቀት-መር ኢኮኖሚ" በሚል መሪ ሐሳብ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል። 


በዚህ ጉባኤ የመክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጉባኤው የሀገራችንን ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶችን ከግልና ከመንግሥት ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ፋይዳው እጅግ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡


ለተደራሽነቱ፣ ለውጤታማነቱና ለቀጣይነቱ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለሥልጣኔ ፈር-ቀዳጅ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቷ ለዚህም የአክሱም ሐውልት፣ የጐንደር ቤተ-መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን፣ የጀጐል ግንብ፣ የጅማ ቤተ-መንግሥት እና ሌሎቹ አመላካች ናቸው ብለዋል፡፡


እነዚህም የትምህርትና ሳይንስ ጥበብ ውጤቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡


መንግሥት ሀገሪቷን ወደ ብልጽግና ማማ ለማውጣትና የሀገሪቷ ቁልፍ ችግር የሆነውን ድህነትን ለመዋጋት የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


በህዝቡ የኑሮ ደረጃ ላይ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦችን ለማምጣት የተለያዩ ፕሮጀክቶችንና ፕሮግራሞችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት የሚተገበር የልማት እቅድ ይዞ ለተግባራዊነቱ ህዝቡን አሳትፎ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል። 


የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ዘርፍ መጠናከር የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማት እንዲሳካ ያስችላልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፤ የፈጠራና የምርምር ሥራዎችን በማበረታታትና እውቅና በመስጠት በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የተመሠረት ምርምርን ማጐልበት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።


ጉባኤውም በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክ ሙያ ተቋማት እንዲሁም ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት የሚያግዙ የእርስበርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠንከር የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ እንዳሉትም ይህ የመጀመሪያው ጉባኤ ቢሆንም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡


በዚህ ጉባኤም ሦስት የሸልማት ዘርፎች የተዘጋጁ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ሙሉ የኢትዮጵያ የሳይንስ ሽልማት፣ የሀገር ልህቀት ሽልማትና የአድናቆት ሰርተፊኬት በመባል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡


ከነዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ የሳይንስ ሽልማት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ሌሎቹ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ይካሄዳሉም ተብሏል፡፡


በዚህ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተሰናዳው ጉባኤ የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤቶችን የማስተዋወቅ እንዲሁም በሥራ ላይ እንዲውሉም ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ተብሏል።

በጉባኤው መክፈቻ መርሃ-ግብር ላይም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ተቋማት፣ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ ተመራማሪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም