ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ባለድርሻዎች መንግስት ከሚመሰርተው ፓርቲ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ባለድርሻዎች መንግስት ከሚመሰርተው ፓርቲ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ምሁራን ተናገሩ
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 5/2013 (ኢዜአ) ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ባለድርሻዎች በምርጫው የህዝብ ይሁንታ ካገኘውና መንግስት ከሚመሰርተው ፓርቲ ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንዳስረዱት፤ በምርጫው የተሳተፉ ፓርቲዎች ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በትብብር መትጋት አለባቸው።
በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት እንዲመሰረትና ለውጡ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻዎች መሆናቸውን ያመለከቱት ምሁራኑ፤ ሕዝቡም በምርጫው ያሳየውን ተሳትፎ በተለይ በምጣኔ ሀብት መስክ ለማጠናከር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው የምርጫውን ውጤት በፀጋ በመቀበል ለውጡን ለማሳካት መተባበር እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ፤ ምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ መጠናቀቁ ታላቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫውያላሸነፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብ ይሁንታ ካገኘው የፖለቲካ ድርጅት ጋር ተቀናጅተው በመስራት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
መንግሥትን ከሚመስርተው ፓርቲ ጋር በመቀራረብ ለሀገር እድገት በሚበጁ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የለውጥ ሥራዎችን እንዲያስቀጥሉም ዶክተር ሀብታሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባለፉት ዓመታት ለይስሙላ ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች አንፃር የዘንድሮው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነው ብሎ መውሰድ እንደሚቻል ያወሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እንዳለ ሙላቱ ናቸው።
ሕዝቡ ይመራኛል የሚለው ፓርቲ መምረጡ አኩሪ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
በድምጻቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የትርምስ አጀንዳ ያመከነው ሕዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀገርን የሚያሻግር መንግሥት ለመፍጠርና ለውጡን ለማስቀጠል መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መግለጫ መሰረት በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን የሕዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች አግኝቷል።
ይህም ፓርቲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለው መሆኑ ታውቋል።