የአዲስ አበባ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ
ሐምሌ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ግድቡ ከፍጻሜ እስኪደርስ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
የግድቡ የሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጀመር ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው የገለጹት፤ አቶ አዲሱ ጌታሁን፤ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ሲያድርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይህንን ድጋፍ በዘላቂነት እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
“የተለያዩ አካላት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ጫና ቢፈጥሩም ሁሉንም ተቋቁመን ግድቡን በራሳችን አቅም ገንብተን እውን እናደርጋለን” ብለዋል።
ጫናውን ለመቋቋም መንግስት የጀመረውን የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ስራ መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።
ሌላው የንግዱ ማህበረሰብ አባል አቶ ጌታቸው ካሳ የአባይ ወንዝ ላይ ልማት ሳይሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በወንዙ ላይ የተጀመረውን ልማት አለመደገፍ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
“አሁን ለእኔ አባይ አንዱ ልጄ ነው ልጄን አለማስተማር ነገውን ከባድ እንደሚያደርግበት ሁሉ በዚህ ወቅት ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ አለማድረግ እኔን ተጠያቂ ያደርገኛል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
በመሆኑም የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ እንደ ነጋዴ ማህበረሰብ አባልና እንደ ግለሰብ አገራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
“ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በመጀመሩ ተደስተናል፤ እንዲጠናቀቅም በጋራ እንሰራለን” ብለዋል።
የግድቡን ግንባታ በራስ አቅም እዚህ አድርሰነዋል፤ እንጨርሰዋለንም ያሉት ደግሞ ከመዲናዋ ነጋዴዎች መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ ቀለመወርቅ ናቸው። በግላቸው ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጓዳኝ የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባባር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።