ቀጥታ፡

በምሥራቅ ወለጋ የተገነቡ የኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ

ነቀምቴ ፤ሐምሌ 05/2013 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከ71 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ።

በዞኑ ጉቶ ጊዳ እና ኡኬ እና ሳሲጋ ወረዳዎች ውስጥ የተገነቡት እነዚህ ሁለት ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያገለግሉ የተለያዩ 27 ክፍሎች እንዳሏቸው በምርቃው ስነ-ስርዓት ወቅት ተገልጿል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለማየሁ ተስፋ በወቅቱ  እንዳሉት፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መጓተት ዓመታትን ያስቆጥር ነበር።

የለውጥ አመራሩ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ግን በርካታ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ እንደተቻለ አመልክተዋል።

በተለይም የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በመደበው ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የበሎና የኡኬ ኢፈ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሰባት ወራት ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ማዘጋጀት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ቤቶቹ የምረቃ ስነ- ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ተወካይ አቶ ታመነ ባልቻ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ስኬታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


በምሥራቅ ወለጋ ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው ብቻ ግብ አይሆንም ያሉት አቶ ታመነ፤ ትምህርት ቤቶቹ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጎች የሚያፈሩ እንዲሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያበረታቱም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የበሎ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀብቴ ኤባ በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻቸው 90 ኪሎ ሜትር መንገድ አቋርጠው በነቀምቴ ከተማ ሲማሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም  ለከፍተኛ ወጪ እና ልጆቻቸውም ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ መንግሥት ችግራቸውን በመረዳት በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት  በመገንባቱ መደሰታቸውን  ገልጸዋል፡፡

በአካባቢያቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባቱ የነበረባቸውን ችግር እንደሚፈታላቸው የተናገሩት ደግሞ የኡኬ ከተማ ነዋሪ አቶ ተጫኔ ደባልቄ ናቸው።  

ልጆቻቸው ትምህርት ቤቱን ተጠቅመው የበቁ  ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም