ቀጥታ፡

ምርጫው ከመነሻው ጀምሮ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነበር- አዲስ ትውልድ ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 05/2013 (ኢዜአ) የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ሂደቱ ከመነሻው ጀምሮ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን አዲስ ትውልድ ፓርቲ ገለጸ።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዘደንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ፤ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ክንውን ተከትሎ የፓርቲያቸውን አቋም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመነሻው ጀምሮ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ጠቅሰው በሂደቱ ዴሞክራሲያዊ የክርክር መድረክ የታየበትና ሰፊ የሚድያ ሽፋን ያገኘ ነበር ብለዋል።

ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው አማራጮቻቸውን ለህዝብ በመሸጥ እመርታ የታየበትና መራጩ ህዝብም በነፃነት እስከ ምሽት ስድስት ሰአት ድረስ የመረጡበት መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫ ሂደቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተምሳሌት ሆኖ አልፏል ብለዋል።

አልፎ አልፎ የተፈጠሩ ችግሮችንም ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በጋራ ምክር ቤት እና ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ለቀጣዩ ምርጫ ብዙ ነገሮችን ተምረን እንድናልፍ አድርጎናል ብለዋል።

አዲስ ትውልድ ፓርቲ በመግለጫው "ኢትዮጵያዊያን ሁለት አገር የለንም አንድ አገር ነች ያለችን ማንም ያሸንፍ፤ አገራችን ኢትዮጵያ የጠላቶቿን አንገት አስደፍታ አሸንፋለች እና ልንኮራ ይገባል" ብሏል።

ፓርቲያቸው የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንደተቀበለው የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ህዝቡም ይህንኑ ተገንዝቦ ለአገር ልማት እና እድገት በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲሁም ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ፍፃሜ እንዲያገኙ አዲስ ትውልድ ፓርቲ የድርሻውን አስተዋፆና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የፓርቲው ጸሀፊ አቶ ክፍለማርያም ኦሪዮ፤ አዲስ ትውልድ ፓርቲ በሁሉም ክልል ለፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤት 174 እጩዎችን አቅርቦ በምርጫው መፎካከሩን አስታውሰዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ባይሆንም ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር በቀጣይ በብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲሁም አገራዊ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራና በትብብር ይሰራል ብለዋል።

አዲስ ትውልድ ፓርቲ በውድድሩ አሸናፊ ለሆነው ፓርቲ መልካም ምኞቱን በመግለፅ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም