ኢዜማ ከስልጣን ይልቅ ለአገርና ለህዝብ ሰላም ቅድሚያ ይሰጣል---አቶ የሺዋስ አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ከስልጣን ይልቅ ለአገርና ለህዝብ ሰላም ቅድሚያ ይሰጣል---አቶ የሺዋስ አሰፋ
አርባ ምንጭ ሐምሌ 04/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከስልጣን ይልቅ ለአገርና ለህዝብ ሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ አስታወቁ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ይህን ያሉት በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል ዛሬ ለህዝብ በተዘጋጀ የምስጋና ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ኢዜማ የራሱን ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል፡፡
ኢዜማ በዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል በማሸነፉ፣ ሴቶች ላደረጉት የነቃ ተሳትፎና ለምርጫው ሰላማዊነትም ሊቀመንበሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
"የዘይሴ ህዝብ በምርጫው ሂደት ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በማሳየት፣ የድምጽ መስጫ ሳጥን በመጠበቅና በድምፅ ቆጠራው ያደረገው እልህ አስጨራሽ ቁጥጥር ለሌላው አካባቢ ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡
ኢዜማ ለአገርና ህዝብ ሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ የሺዋስ፣ ስልጣንም ሆነ የህዝቡ ጥያቄ መመለስ የሚቻለው አገር ሰላም ሲሆን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫው ዙሪያ ያሉ ማንኛውንም አይነት ችግሮች በህጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ፓርቲያቸው መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በፓርቲዎች መካከል የሃሳብ ልዩነት እንጂ የአገር ልዩነት ባለመኖሩ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩ ኢዜማ ከመንግስት ጋር አብሮ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
አቶ የሺዋስ በአገራዊ ምርጫ ኢዜማ በዜይሴ ልዩ ምርጫ ክልል እንዲያሸንፍ ለመረጠውም ሆነ ላልመረጠው ህዝብ እንዲሁም በምርጫው ለተሸነፉ ፓርቲዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በዘይሴ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር አሸናፊ የሆኑት አቶ አብርሃም አቦሼ በበኩላቸው ኢዜማን ለመረጠው ህዝብ እንዲሁም በሃሳብ፣ በጊዜ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ለደገፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ያለትግል ነፃነት እንደማይገኝ የገለጹት አቶ አብርሀም፣ "ነፃነት ሲኖር የዜጎች ማንነት፣ ሉዐላዊነት፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና ሁለንተናዊ ልማት በቀላሉ ይረጋገጣል" ብለዋል፡፡
የዘይሴ ህዝብ ለ47 ዓመታት የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርብ ቢቆይም አስከዛሬ ምላሽ እንዳላገኘ ጠቅሰው፣ በቀጣይ ይሄና መሰል የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡
"6ኛው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ነበር፤ ዴሞክራሲን በአገራችን ለማረጋገጥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል" ያለው ደግሞ ወጣት አማኑኤል ገብረሚካኤል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስፈን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆርጠው እንደተነሱ ሁሉ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ያሉ አመራሮችም ከእሳቸው መማር ይኖርባቸዋል" ብሏል፡፡
ወይዘሮ ውባየሁ ተፈሪ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "6ኛው አገራዊ ምርጫ እንደአገር ዴሞክራሲያዊና ሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት የተስተናገዱበት ነው" ብለዋል።
በምርጫው ምንም እንኳን ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩም ከሌሎች ምርጫዎች አንፃር የተሸለ ሰላማዊና ፍትሃዊ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ውባየሁ፣ የዘይሴ ሴቶች በምርጫው ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ ለሌሎች አርአያ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ያልተለመደ ባህል ለመፍጠር የተዘጋጀው የምስጋና ፕሮግራም በፓርቲዎች መካከል በቀጣይ እንደ ባህል መለመድ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡