የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የቅደመ መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት ይደረጋል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የቅደመ መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት ይደረጋል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ሀምሌ 4/2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅድመ መደብኛ ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ዘርፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርና የፕሮጀክቶች ጉብኝትና ምርቃት አካሂዷል።
ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ማለዳ በቢሾፍቱ ከተማ በመገኘት የትምህርት ዘርፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመዋለ ህጻናት ትምህርት ቤት ግንባታና የጎልማሶች ትምህርትን አስጀምረዋል።
ክልሉ በዚህ ክረምት ከሚያስፈልጉት 12 ሺህ መዋለ ህጻናት ትምህርት ቤት መካከል 3 ሺህ ትምህርት ቤቶችን በበጎ ፈቃድ ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋና አላማው ትውልድን መገንባትና ዜጎች በጋራ ልማትን እንዲያፋጥኑ በማሰብ የሚከወን ነው ብለዋል።
ክልሉ ባለፈው ዓመት በበጎ ፈቃድ አገልግሎ አማካኝነት 34 ሺህ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት መቻሉንም አስታውሰዋል።
በዚህ ክረምትም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ከመዋለ ህጻናት መጀመሩ ተገቢ በመሆኑ 3 ሺህ ትምህር ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹን ለመገንባት እስካሁን ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ከ3 ሚሊዮን በላይ ጎልማሶችን ለማስተማር ከመቶ ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት እንደሚሰማሩም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ፤ የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ሁሉም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የማዋለ ህጻናት ትምህርት ቤቶቹ መገንባት እንዳለ ሆኖ የመጽሃፍት ድጋፍ በስፋት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ 'ኢፋ ቦሩ' ተብለው የተሰየሙ ከመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መመረቃቸውንም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል በትምህርት ዘርፍ የጀመረውን ስራ ሌሎች ክልሎችም ሊከተሉት ይገባል ያሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጀነር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው።
ሁሉም ክልሎች በስፋት የመዋለ ህጻናት ትምህርት ቤቶችን ቢገነቡ ለአገሪቷ ትልቅ መሰረት እየጣሉ መሆኑን መረዳት አለባቸው ነው ያሉት።
ክልሎች የቀጣይ ዓመት በጀታቸውን ሲይዙ ለዚሁ ጉዳይና ለትምህርት ቤት ምገባ ታሳቢ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በኋላ በዱከም ከተማ የተገነባውንና 40 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን 'የኢፋ ቦሩ ኦባይ ዲብዲቤ' ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን መርቀዋል።
በአካባቢው የአርሶ አደር ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማግኘት ርቀው ይጓዙ የነበረ በመሆኑ የትምህርት ቤቱ መገንባት ችግሩን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ በስድስት ወራት የተጠናቀቀ ሲሆን በመጪው መስከረም ተማሪዎችን የሚቀበል ይሆናል።
ከትምህርት ቤቱ ምርቃት በሻገር የዱከም ከተማን ለማስዋብ እየተሰሩ ያሉ ስረዋችንም አቶ ሽመልስ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የቢሾፍቱና የዱከም ከተማ ነዋሪዎች ለፕሬዚዳንቱና ባልደረቦቻቸው የተለያዩ ስጦታዎችንም አበርክተዋል።