ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!

33

በሰለሞን ተሰራ ኢዜአ

በትግራይ ያለው የህወሓት አንጃ ጠብ-አጫሪነት እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ወቅት የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በተለይ አሜሪካ መራሾቹ ጉዳዩን በማስጮህና በማጋነን ትኩረት ለመሳብ በሚያደርጉት ጥድፊያ የሚቀድማቸው አጥተዋል፡፡

እነዚሁ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ በኢትዮጵያ ስለተከናወነው ሰላማዊ የምርጫ ሂደት አንድ መስመር ለመጻፍ አልፈቀዱም ይለናል ግራሃም ፔብልስ የተባለው ጸሐፊ፡፡

የምርጫ ሂደቱ የተዋጣለት ነው ማለት ባይቻልም ምርጫውን ተከትሎ ቀውስ ስለመፈጠሩ የቀረበ አንድም ሪፖርት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሂደቱ ጥሩ እንደነበር ሲያስታውቅ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ችግር እንደነበረበት በቅሬታ አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች በበኩላቸው ምርጫው በስነ-ሥርዓት በተቀመጠለት አግባብ ሰላማዊና ተአማኒ በሆነ መንገድ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶችና በቁሳቁስ አቅርቦት ችግር 100 በሚጠጉ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ያልተከናወነ ሲሆን ሂደቱን በማስተካከል በጳጉሜ ወር መጀመሪያ ላይ ድምጽ የሚሰጡበት አግባብ ተመቻችቷል፡፡

በአንድ የግል ተወዳዳሪ አቤቱታ ምክንያት ምርጫ ቦርድ ያቋረጠዉ የነጌሌ ምርጫ ሐምሌ 2 ቀን ተከናውኗል። የነጌሌ የምርጫ ክልል አስተባባሪ የምርጫው ሂደት በ30 የምርጫ ጣቢያዎች መከናወኑን ለአሜሪካ ድምጽ ገልጸዋል።

የትግራይ ሁኔታ ያለየለት በመሆኑ የምርጫ ሂደቱን አሁን ላይ መናገር አዳጋች ነው፡፡

የምርጫ ሂደቱ በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን በቀጣይ ዴሞክራሲን የተላበሰ መንግሥት ለመመስረት መሠረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ብዙዎችን ባስደነቀ መልኩ ገዥው ፓርቲ በምርጫው አሸናፊ ሆኗል፡፡ ምርጫው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት ዥንጉርጉር ምክር ቤት ለማየት እድል ባይሰጥም በመንግሥት አደረጃጀትና የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን እንደሚያካትቱ አስታውቀዋል፡፡

በምርጫ ሂደቱ የታየው ጠቅላይ አሸናፊነት አሳዛኝና ጤናማ ባይሆንም አሸናፊው መንግሥት ታላቅ ኃላፊነት የወደቀበት መሆኑን አውቆ አጋጣሚውን በመጠቀም ለህዝቡ አንድ ታሪክ ጥሎ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡

ጣልቃ-ገብ  አካላት

አገሪቱ በበርካታና ጊዜ በማይሰጡ አንገብጋቢ ችግሮች ተወጥራ ባለበት በዚህ ወቅት የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡

በቅድሚያ የትግራይን ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚገባ ሲሆን ለዚህ ስኬት ደግሞ የህወሓት ኃይሎች ተባባሪነት ወሳኝ ነው።

በተጨማሪ በየቦታው ብቅ ጥልቅ የሚሉትን የብሄር ግጭቶች ማስቆምና ኢኮኖሚውን ወደፊት ማራመድ መቻል ወሳኝ ተልዕኮዎች ናቸው፡፡

በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለማርገብ መንግሥት የራሱን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በማውጣት ለተግባራዊነቱ እየተጋ ቢሆንም የህወሓት አሸባሪ ቡድን ምላሽ ግን ወደ ባሰ አዘቅት የሚከት መሆኑ እየታየ ነው፡፡

ቡድኑ በአጎራባች ክልሎችና ጎረቤት አገራት ላይ ጦር ለመስበቅ መዘጋጀቱን በአደባባይ እየገለጸ ይገኛል፡፡

የሰብዓዊ አቅርቦቱን በተመለከተ መንግሥት ያሳወቀውን የተረጂ ቁጥር በተመለከተ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የሚያወጡት አሃዝ የሚጋጭ ነው፡፡ ይህንኑ በማስተጋባት ደግሞ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንን የሚቀድማቸው አልተገኘም፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በመጀመሪያው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ በሁለተኛውና ሦስተኛው ዙር ድጋፍ ደግሞ ለ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከጦርነቱ ጋር ተዳምሮ የተረጋገጠ መረጃ ለማግኘት አዳጋች መሆኑ እየታወቀ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንና ቃል አቀባዮቻቸው የሚያወጡትን መረጃ ከየት እንደሚያገኙት ለማወቅ ያዳግታል፡፡

በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የምዕራባውያን ተቀላቢ መገናኛ ብዙኃን በቦታው ሳይገኙ የተበተነላቸውን ውሸት በማፈስ ደጋግመው ያናፍሱታል፡፡ ነገር ግን ይህን ተግባራቸውን ለምን እንደሚፈጽሙ ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡

የአፍሪካ ህብረት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በክልሉ ያለውን ሁኔታ የሚያጠና መርማሪ ቡድን ማዋቀሩ ይታወቃል፡፡

መንግሥት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ለሰላማዊ ውይይት በር ከፋች ቢሆንም ከህወሓት አሸባሪ ቡድን ግን ተመሳሳይ ምላሽ ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ የአሜሪካንና የአውሮፓውያንን አካሄድ በመቃወም ቁጣቸውን አሰምተዋል፡፡

በማርች 21 ቀን 2021 የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ለአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ባደረጉት ንግግር “ጉዳዩን በተመለከተ ገለልተኛ የሆነ ማጣራት እንዲደረግ እንፈልጋለን፤ እንዲሁም የሁለትዮሽ ስምምነት መከናወን አለበት” በማለት ተናግረዋል፡፡

ስምምነት የሚደረገው አገሪቱን ለ 27 ዓመታት በአምባገነንነት ካስተዳደረውና አገሪቱን ሲዘርፍ ከኖረው ከህወሓት ጋር ነው ?  በማለት ፀሐፊው ይጠይቃል፡፡

የአሜሪካንን ማዕቀብና ተረክ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ “በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ሙከራ የሚደረግ ከሆነና የሁለቱን አገራት ለክፍለ ዘመን የዘለቀ ወዳጅነት ለማጣጣል ከተሞከረ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለመመልከት ይገደዳል”ብሏል፡፡

አሜሪካና ወዳጆቿ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እያሳዩ ያሉት ጣልቃ-ገብነት በርካታ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ ያስቆጣ ነው፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ዘንድ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት አሁንም የምዕራባውያኑ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ አገሪቱን ለ 27 ዓመታት በኢህአዴግ ስም ሲገዛ የነበረው አምባገነኑ ቡድን በህዝብ ተቃውሞ ከሥልጣኑ ተወግዷል፡፡

ሁሉንም ጠቅሎ ሲገዛ የኖረውና ማንም ይቅር የማይለው ህወሓት አገሪቱን በፍርሃት ሲንጥ ከመቆየቱ ባለፈ ህዝቡን በብሄር በመከፋፈል ሲያናቁር መኖሩ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ሙስና መገለጫው የሆነው የህወሓት ቡድን የመንግሥትን ወጪ በመመዝበር፣ ህዝቡን በብሄር በመከፋፈል፣ መንግሥታዊ ሽብር በመፈጸምና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችና ብሄሮች ላይ ሰብዓዊ ወንጀል በማድረስ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡

ህወሓት ይሀንን ሁሉ ግፍ እያደረሰ አገር ሲያስተዳድር በነበረበት ወቅት እንኳ የምዕራባውያኑ ድጋፍ ያልተለየው ሲሆን በተለይ አሜሪካና እንግሊዝ እስከ መጨረሻው ህቅታ ድረስ ከአጠገቡ አልተለዩም፡፡

አሁንም ይህንን የተተፋ ቡድን ወደ ሥልጣን ለመመለስና ኢትዮጵያ የቀጠናው ነፃና የበላይ አገር ለመሆን የጀመረችውን ጥረት ለማደናቀፍ  እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በመላ አገሪቱና በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደጋግመው ” በሉዓላዊ አገር ላይ የሚደረገው ጣልቃ-ገብነት ይቁም “በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የቡድን ሰባት አገራት ለንደን ላይ ባደረጉት ስብሰባና በዋሸንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ታላላቆቹ ምዕራባውያን ሚዲያዎች ሽፋን አልሰጧቸውም። በአንፃሩ “ሰብዓዊ ሁኔታዎች” በሚል (ስለጉዳዩ የሚያውቁት ጥቂት ቢሆንም ) በትግራይ ያለውን ሁኔታ አግዝፈው ለማውጣት ጥረት አድርገዋል፡፡

እንደ ቢቢሲ፣ ሲኤን.ኤን፣ ዘ ጋርዲያን፣ አልጀዚራ እና ቪኦኤን የመሳሰሉ ግዙፍ የመገናኛ ብዙኃን የምዕራባውያን መንግሥታት የፕሮፓጋንዳ ማሽን በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተከናወነውን ምርጫ በተመለከተ የሰሩት ዘገባ በአብዛኛው አሉታዊ ነገሮች ላይ ያተኮረና የምዕራባውያንና የአሜሪካንን አጀንዳ ለማሰራጨት ያለመ መሆኑን መታዘብ ተችሏል፡፡

የዚህ ድምጸት አጠቃላይ መዳረሻ ለኢትዮጵያውያን ግልጽ ነው፡፡ ይህንኑ አሉባልታ በማስተጋባት ላይ የሚገኙት፣ ሱዛን ራይስ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና የባራክ ኦባማ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን የሰሩ ናቸው፡፡

አሁን ላይ ደግሞ የህወሓትን ማፊያ ቡድን በመወከል የባይደንን አስተዳደር ለማሳመን እየሰሩ ሲሆን ይህንኑ ቡድን እሳቸውም ሆኑ ኦባማ ሲደግፉት መኖራቸው ይታወቃል፡፡

ታላቋ አሜሪካ ያለምንም ሃፍረት አሸባሪውን ቡድን በአምባገነኑ የግብጽ መንግሥት በኩል መሳሪያ እያስታጠቀች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ እምቅ አቅም

ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ መንገድ በማለፍ በአስደናቂና በእምቅ የሽግግር ሂደት ውስጥ ትገኛለች። በዚህም ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ብርሃን እየተጓዘች ነው፡፡

በህወሓት ዘመን ያልነበረ የመናገር ነጻነትና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመታከት እየሰራችም ትገኛለች፡፡

በማንኛውም የዴሞክራሲ ትግበራ ሂደት ውስጥ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች የማይጠፉ በመሆኑ መንግሥትም እነዚህን ማነቆዎች ለማለፍ በራሱ መንገድ አማራጮችን ዘርግቶ እየሰራ ነው፡፡

ይህንኑ ብሩህ ተስፋ ለማጨለምና ኢትዮጵያን በመበታተን የብሄር ክፍፍልና ግጭት ለማስነሳት ግብጽንና ሱዳንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገራት በጋራ ተሰልፈው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ግብጽና ሱዳን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ በመቃወም አገሪቱን ለማዳከም ቆርጠው የተነሱ ሲሆን፤ ምክንያታቸው ደግሞ የአገሪቱ እድገትና ለውጥ በቀጠናውና በአህጉሪቱ ያለውን የኃይል መሪነት ለኢትዮጵያ እንደሚያጎናጽፍ መረዳታቸው ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ አገሪቱ በቅኝ አለመገዛቷ፣ በርካታ ጥንታዊ ባህል ያላት መሆኗና ከቻይና ጋር የመሠረተችው ወዳጅነት ጥርስ ውስጥ አስገብቷታል፡፡

የቀደሙት አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎችና ጊዜ እያለፈበት የመጣው የአሜሪካ ኃይል ኢትዮጵያ እንድታብብ የማይፈልጉ ሲሆን ዘወትር የአውሮፓ እርዳታ ጥገኛ ሆና መመልከቱን ይፈልጉታል፡፡

አገሪቱ ወደፊት የምታደርገውን ጉዞ ለማሳመር ወዳጅ የሚያስፈልጋት መሆኑ ባይካድም እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና አውሮፓ ህብረት ያሉ በራሳቸው ፍላጎት የታጠሩ ሙሰኞችን ግን አትሻም፡፡

እነዚህ አገራት ለሦስት አሥርት ዓመታት የህወሓትን የግድያ፣ የስቃይና የዝርፊያ ተግባር አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ የኖሩ ናቸው፡፡

ህወሓት ለአምስት ጊዜ ምርጫን በማጭበርበር ህጋዊ አስመስሎ ሲያቀርብ ትንፍሽ አላሉም፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብን ለለውጥ፣ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ለመሥራት ከልቡ ተነስቷል፡፡

በዐቢይ አህመድ ለሚመራው የብልጽግና ፓርቲም ይሁንታውን በመስጠት ለውጡን ለማሳካት አብሮ ተሰልፏል፡፡

ፓርቲው ሥልጣን ላይ ከሚወጣበት የመጀመሪያዋ እለት አንስቶ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ተግባራትንና ስኬቶችን ስለሚጠብቁ አይናቸውን ከፓርቲው ላይ እንደማይነቅሉ አያጠያይቅም ፡፡

ባለፉት አሥርት ዓመታት በተጠና መንገድ ስትከፋፈል የቆየችውን አገር ወደ አንድነት ለማምጣት ጊዜ፣ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ትዕግስት ይጠይቃል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ቅንነትንና ታማኝነትን ማንጸባረቅ ከተቻለ በጊዜ ሂደት መተማመን እየሰፈነ መከፋፈል ይከስማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም