ጸጥታው ምክር ቤት መልስ ለእውነትና ለፍታዊነት መቆም በዓለም አደባባይ አሸናፊ እንደሚያደርግ ትምህርት የተገኘበት ነው--የሲቪክ ማህበራት

ባህር ዳር  ሐምሌ 3/2013 (ኢዜአ) የጸጥታው ምክር ቤት የሰጠው መልስ ለእውነትና ለፍታዊነት መቆም በዓለም አደባባይ ጭምር አሸናፊ እንደሚያደርግ ትምህርት የተወሰደበት ነው ሲሉ ሁለት የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።

የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ መወሰኑም የኢትዮጵያን ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚል አቋም አሸናፊነት እንደሚያሳይም ተናግረዋል።    

የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ሞላ ደሴ ለኢዜአ እንዳሉት ግብጽና ሱዳን በጋራ ከመልማትና ከመጠቀም ይልቅ "እኔ ብቻ ልጠቀም" የሚል ግትር አቋማቸውን ይዘው ቀጥለዋል።

ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና አፍሪካዊ መፍትሄን ወደጎን በማለት ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት መፈታት አለበት በማለት ሲንቀሳቀሱም ቆይተዋል።

የታችኛው ተፋሰስ ሀሳባቸው የዓባይ ውሃን 86 በመቶ ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያን ያገለለና የእነሱን ጥቅም ያስቀደመ በመሆኑም በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሃሳብ ጎልቶ መውጣቱን ተናግረዋል።

የሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሀሳብ ለ21 ኛውን ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑንም አቶ ሞላ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ መልስ በፍትሀዊነት ለእውነት መቆም በዓለም አደባባይ ጭምር አሸናፊ እንደሚያደርግ ትምህርት የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ እምነት መኖሩን ከማሳየተ ባለፈ የኢትዮጵያንም አቋም ከፍ እንዲል ማድረጉን አመልክተዋል።

"በተለይ ኢትዮጵያ የእኩል፣ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት አጀንዳ ይዛ መቅረቧ፤ አፍሪካዊ መፍትሄ፣ አብረን እንልማ እና እንደግ ማለቷ በዓለም አደባባይ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ አስችሏታል" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ስራ ከጀመረች ጀምሮ እስካሁን ድረስ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጫና ሲፈጠርባት ቆይተዋል" ያሉት ደግሞ የአማራ ሴቶች ማህበር ዋና ፀሐፊ ወይዘሮ ትጥቅነኝ አለሙ ናቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ ሊዳኝ ይገባል በሚል በያዘችው ፅኑ አቋም ድርድሩ ተመልሶ በአፍሪካ ህብረት እንዲካሄድ መደረጉ  የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

"የግድቡ 2ተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለቀጠናው የደህንነት ስጋት ነው በሚል ጉዳዩን ዓለም አቀፍ በማድረግ ጫና እንዲደረግባት ጥረቶች ቢደረጉም ይህም አይሳካም" ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ በእኛ ዘመን የተደገመ ሌላኛው የአድዋ ድል ነው በማለትመ ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ ህብረት ሦስቱን ሀገራት እኩል ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለጉዳዩ እልባት በመስጠት በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ወይዘሮ ትጥቅነኝ ጠይቀዋል።

"የምክር ቤቱ መልስ ኢትዮጵያዊያን እውነትን ይዘው በህብረት ከቆሙ አሁን የተጋረጡትን ፈተናዎች ማሸነፍ እንደሚችሉ ትምህርት የተወሰደበት ትልቅ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም