የህዳሴ ግድቡ ሰራተኞች ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ የጸጥታው ምክር ቤት የወሰደው አቋም ተጨማሪ ብርታት እንደሚሆናቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድቡ ሰራተኞች ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ የጸጥታው ምክር ቤት የወሰደው አቋም ተጨማሪ ብርታት እንደሚሆናቸው ገለጹ
ሐምሌ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የግብጽና የሱዳንን ኢ-ፍትሀዊ አካሄድ ከማሳየት ባለፈ ለስራችን ተጨማሪ ብርታት ሰጥቶናል” ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰራተኞች ገለጹ።
የአፍሪካ ሀገራት ለችግሮቻቸው አፍሪካዊ መፍትሄን ማስቀደም እንዳለባቸውም ትምህርት የሰጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርቡ በፀጥታው ምክር ቤት በቀረበው የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የሦስትዮሽ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ በምክር ቤቱ አቋም ተይዟል።
ኢዜአ የግድቡ ግንባታ በሚካሄድበት ጉባ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የፕሮጀከቱ ሠራተኞች እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ አቋም ለስራቸው ተጨማሪ ብርታት ሆኗል።
መድረኩ የግብጽ እና የሱዳን አካሄድ ፍትሃዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ለዓለም ያሳየ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከግድቡ ሠራተኞች መካከል አቶ ሃይሉ ካሳዬ እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ለግድቡ ስኬት ሌት ተቀን እየሠሩ ነው፡፡
"የጸጥታው ምክር ቤቱ የወሰደው አቋም ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች ተጨማሪ ሞራል ሆኗል" ያሉት አቶ ሃይሉ፤ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ አበበ ተሻገር የተባሉ ሌላው የግድቡ ሠራተኛ በበኩላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ያለመብራት በጨለማ እየኖሩ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ግብጽ እና ሱዳን ይህን እውነታና የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ህዝባቸው እንዲያውቅ ፈጽሞ እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት።
"ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ መጠቀም በተመለከተ በየትኛውም መድረክ እውነታውን ይዛ ነው የምትሟገተው" ያሉት አቶ አበበ፤ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊያን በራሳቸው እንደሚፈቱ ያስተማረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግድቡን ለፍጻሜ ከመብቃት ወደ ኋላ የሚመልስ ነገር እንደማይኖር የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸው፣ “በሰራተኛው ላይ የተፈጠረው መበረታታት እስከ መስዋዕትነት ለመክፈል ያነሳሳ ነው” ብለዋል።
"መጀመሪያም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ እንደሌለበት ሁሉም የሚረዳው ሃቅ ነው" ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ታምሬ ሙሉነህ የተባሉ የፕሮጀክቱ ሠራተኛ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ ጉዳዮን በአፍሪካ ህብረት ለውይይት እንዲቀርብ መወሰኑ በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
“በጸጥታው ምክር ቤት የተወሰደው አቋም ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ለችግሮቻው በራሳቸው መፍትሄ መፈለግ እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ነው” ብለዋል፡፡
በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የሃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንዳልሆነች የገለጹት ኮሎኔል ታምሬ፤ ሃብቷን በማልማት ለመጠቀም እያደረገችው ያለው ጥረት ወትሮም በተለየ ሁኔታ መታየት እንደሌለበት አመላክተዋል።
የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ መወጣት የሚቻለው በአንድነት ሲቆም መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ መሃሪ አንተነህ የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ትውልዱ የራሱን አኩሪ ታሪክ የሚያስቀምጥበት መሆኑን ተናግረዋል። የግብጽ እና ሌሎች ሃገራት ስጋትም ኢትዮጵያ ወደ ልማት የምታደርገው ይሄው ጉዞ እንደሆነ አቶ መሃሪ ለኢዜአ አክለው አስረድተዋል፡፡