ኢዜማ ለዘይሴ ህዝብ ያዘጋጀው የምስጋና ስነ-ስርአት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ለዘይሴ ህዝብ ያዘጋጀው የምስጋና ስነ-ስርአት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ እየተካሄደ ነው
አርባ ምንጭ፣ ሐምሌ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ለዘይሴ ህዝብ ያዘጋጀው የምስጋና ስነ-ስርአት እየተካሄደ ነው።
የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ኢዜማ ዜጋ ተኮር ፌዴራሊዝም ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ፓርቲ በመሆኑ ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በፓርቲው እንደታሰበው ብዙ የምርጫ ክልሎች ላይ ፓርቲው እንዳላሸነፈ ገልጸዋል።
"ካሸነፍንባቸው ጥቂት አካባቢዎች አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዘይሴ ልዩ ምርጫ ክልል አንዱ በመሆኑ ለህዝቡ ምስጋና ለማቅረብ መድረክ ተዘጋጅቷል" ብለዋል።
ምርጫው በአግባቡ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የህዝብን ድምፅ በፀጋ ለመቀበልና ችግሮችንም በህጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በምርጫው ምክንያት ሀገርና ህዝብ አደጋ ላይ መውደቅ እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።
"የመረጠን የዘይሴ ህዝብ ምስጋና ይገባዋል" ያሉት አቶ የሺዋስ፤ መንግስትን ጨምሮ የምርጫ አስፈፃሚዎችና ታዛቢዎች ለምርጫው ሰላማዊነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
በስነ-ስርአቱ ላይ የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘይሴ ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ተገኝተዋል።