ቀጥታ፡

"የወታደር ልጅ ነኝ" በሚል ርዕስ የተጻፈ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀረበ

ሐምሌ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የወታደር ልጅ ነኝ" በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ ሻለቃ የወይንሐረግ በለጠ የተጻፈ መጽሐፍ ተመርቆ ለአንባቢያን ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መጽሐፉ ሲመረቅ ደራሲዋ የወይንሐረግ እንደገለጸችው፤ የውትድርና ሕይወት ምን እንደሆነ መፅሃፉ ግንዛቤ ይሰጣል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ግጥምና አጭር ልቦለዶችን ትጽፍ እንደነበር አስታውሳ፤ ግጥሞቿና አጫጭር ልቦለዶቿ በመጽሐፍ መልክ መውጣታቸው ለቀጣይ ሥራ ብርታት እንደሆናት ተናግራለች።

በመጽሐፉ ላይ የተካተቱት ሁለት አጭር ልቦለዶች በፊልም መልክ መሰራት እንደሚችሉ እና ሐሳቡ ተጀምሮ እንደነበርም ገልጻለች።

በመጽሐፍ ምርቃቱ ላይ ተገኝቶ ሐሳቡን የሰጠው ፀሐፊ ተውኔት እና አዘጋጅ ኃይሉ ፀጋዬ በሀገራችን ወታደር በሚገባው ልክ ትኩረት እንዳላገኘ ተናግሯል።

“መጽሐፉ የወታደር ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ያስገነዝበናል” ብሏል።

አርቲስት ተስፋዬ ማሞ በበኩሉ የደራሲዋን ተሰጥኦ ረዘም ላለ ጊዜ ሲከታተለው እንደነበርና  ሥራዎቿንም ቀደም ብሎ ያውቃቸው እንደነበር ገልጿል።

"የወታደር ልጅ ነኝ" የተሰኘው መጽሐፍ 120 ገጾች ያሉት ሲሆን ግጥሞችና ሁለት አጫጭር ልቦለዶች ተካተውበታል።

ደራሲዋ “የመጽሐፉ ማስታወሻነት ባሎቻቸው በጦር ሜዳ ወድቀው ልጆቻቸውን ለብቻቸው ላሳደጉ እናቶች ይሁንልኝ” ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም