ቀጥታ፡

የሪጅኑ ሰራተኞች በ14 ሄክታር መሬት ላይ አረንጓዴ አሻራቸውን የሚያሳርፉበትን ችግኝ ተከላ ጀምረዋል

ጅማ፣ ሀምሌ 4/2013 (ኢዜአ) የኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሪጅን ሰራተኞች ዘንድሮ በ14 ሄክታር መሬት ላይ አረንጓዴ አሻራቸውን የሚያሳርፉበትን የችግኝ ተከላ ጀምረዋል።

ሰራተኞቹ በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ በተረከቡት 14 ሄክታር መሬት ላይ የዛፍ ችግኝ ተከላ ጀምረዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ካሳ  ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ አመት 62 ሺህ ችግኞች በሰራተኞች ይተከላሉ።

የሪጅኑ 400 የሚደርሱ ሰራተኞች ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ችግኝ ተከላውን ከትላንት ጀምሮ እያካሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት ለተተከሉ ችግኞች ክትትልና እንክብካቤ በመደረጉ 94 በመቶው መፅደቃቸውን ተናግረዋል።

በዚህ አመት ለችግኝ ተከላ ስራ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኢትዮ-ቴሌኮም የፋይናንስ ማናጀር ወይዘሮ ዘውድነሽ ብሩ ናቸው፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በጅማ ዞን በዴዶ ወረዳና በጅማ ከተማ አካባቢ ለተተከሉ ችግኞች ሰራተኛተመድበው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት ማናጀሯ  3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የእንክብካቤ ስራው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የቀርሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነጂብ አባራያ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ችግኝ በመተከሉ የወረዳው ህዝብ  ተጠቃሚ መሆኑን  ገልፀው ዛሬም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የተከላ ስራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የኩባንያው ሰራተኛ ወይዘሮ ቀለሟ መገርሳ በሰጡት አስተያየት "ዛፍ መትከል ለልጅ ልጆቻችን የሚተላለፍ ቅርስ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡

ለምለምና ውብ አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የተናገሩት  ወይዘሮ ቀለሟ ቀደም ሲል በነበሩ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች ላይ ተገኝተው ችግኝ መትከላቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ የሪጅኑ ሰራተኛ ወይዘሮ መሰረት ሙሴ በበኩላቸው "ችግኝ በመተከሉ አፈራችን ከመሸርሸር ይጠበቃል፣ አየራችን የተስተካከለ ይሆናል፤ በመሆኑም በጋራ ወጥተን  በትብብር እየተከልን ነው" ብለዋል፡፡

"ሁሉም በየአካባቢው ችግኝ መትከል ቢችል የበለጠ መልካም ይሆናል" ያሉት ወይዘሮዋ ተከላው ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም