በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ለተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ለተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸነፈ
ሀምሌ 3 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተካሄደው ስድስተኛ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን አሸንፋል።
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወዳደሩ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ መንግሰት መመስረት እንደሚችል ይታወቃል።
በስድስተኛ ጠቅላላ የምርጫ ውጤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በመድረኩም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና የሲቪክ ማህበራት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርገዋል።
ዛሬ ይፋ በሆነው የምርጫ ውጤት መሰረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት 484 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 410 መቀመጫ ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
በዚሁ መሰረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብን 5፣ ኢዜማ 4፣ የግል ተወዳዳሪዎች 4 እንዲሁም የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 2 ወንበር ማግኘታቸው ይፋ ሆናል።
በኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ መንግስት መመስረት ይችላል።