አገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
አገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
ሐምሌ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ አገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው” ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ።
የ6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንቷ ባደረጉት ንግግር፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የቦርዱ አባላትና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።
ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮችን ተቋቁሞ ድል ማስመዝገብ መቻሉን አድንቀዋል።
በምርጫው ላሸነፉ ፓርቲዎችን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈው፤ በዚህ ምርጫ ያልተሳካላቸው ፓርቲዎች በቀጣይ የተሻለ ዕድል እንደሚኖር መገንዘብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ፓርቲዎች ያሏቸውን ማንኛውም አቤቱታ ህጋዊ መንገድን በመከተል ሊያቀርቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዶፍ ዝናብ፣ ፀሐይና ምሽት ሳይበግረው ‘ድምጼ ያስፈልጋል’ ድምጽ ለሰጠው ህዝብ ያላቸውን አክብሮት የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ “በማንኛውም የምርጫው ሂደት ዋናው አሸናፊ ሆኖ መውጣት ያለበት አገር ነው” ብለዋል።
“በመሆኑም ኢትዮጵያችን አሸናፊ ሆና በመውጣቷ ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ከምርጫ በኋላ ያለው ስራ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አመልክተው፤ “አሸናፊው ወገን የሚመሰርተው መንግስት ኢትዮጵያውያንን በሙሉ በእኩልነት የሚያስተዳድር እንደሚሆን ይጠበቃል” ብለዋል።
“አገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ የማይጥምም ሃሳብ ቢሆን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
“በጋራ ጉዳይ ስንወያይ፣ ስንከባበር፣ በሃሳብ ስናሸንፍ ወይም ስንሸነፍ፣ ካልተግባባን ላለመግባባት ስንስማማ፣ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሳንለያይ ብሔራዊ መግባባት ሲኖረን፣ እንድነታችንን ስናጠናክር፣ ለሁሉም መብቶች መከበር ስንቆም፣ ስናከብር፣ ስናስከብር ብቻ ነው በጋራ የምንጽፈው ምዕራፍ ጥሩ ሊሆንልን የሚችለው” ሲሉ አስረድተዋል።