ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የፀጥታ ችግሮችን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 03/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የውስጥና ድንበር ዘለል የፀጥታ ችግሮችን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በቦንጋ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ለአምስት ወራት ያሰለጠናቸውን 350 ልዩ ኃይል ፖሊሶች ዛሬ አስመርቋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ በማድረግ እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከሩ ተግባር ይቀጥላል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት የማይሹ የውጪና የውስጥ ባንዳዎች በክልሉ የሰላም ችግር ለመፍጠር ጠንስሰውት የነበረው ሴራ በጸጥታ አካላትና በህዝቡ የጋራ ጥረት ሳይሳካላቸው መቅረቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጸጥታ መዋቅር አደረጃጀቱ በማጠናከር የዜጎችን ሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲ መብትና የህግ የበላይነትን የማረጋገጡ ተግባር  እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ክልሉ ጠረፋማና ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ የሚፈጸሙ ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብት ዘረፋ ወንጀሎችን የመግታቱ ተግባርም ሌላው የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።

የዕለቱ ተመራቂዎች በአምስት ወራት ቆይታቸው በተግባርና በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን የህግና ጸጥታ ማስከበር ስልጠና ወደ ተግባር በመለወጥ ህዝቡን ከአድሎ በጸዳ መልኩ ማገልገል እንዳለባቸው ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው፤ ክልሉ ሰፊ የደንበር ወሰን ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች በተጨማሪ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የሰዎች ዝውውር መኖሩን ተናግረዋል።

እነዚህን ድንበር ዘለል ወንጀሎችና የውስጥ ፀረ- ሰላም ኃይሎችን ለመከላከል የልዩ ኃይል፣ የመደበኛና የሚሊሻ ጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር የተለያዩ የጸጥታ ፈተናዎች ባሉባት ወቅት የተመረቁ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው  ያሳሰቡት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር ናቸው።

ተመራቂዎች በሰጡት አስተያየት መንግስትና ህዝብ የጣለባቸው ህግ የማስከበር ኃላፈነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ  ከክልሉ ከፍተኛ የሰራ ኃላፊዎች ጋር ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም