በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ለመቋቋም ዲያስፖራው የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኤጀንሲው - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ለመቋቋም ዲያስፖራው የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኤጀንሲው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) በታላቁ ህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ለመቋቋም የዲያስፖራው ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግድቡ ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመቀልበስ ጥረቱን እንደሚቀጥልም ኤጀንሲው ገልጿል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዜጎችን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት አገሪቷንም ከድህነት ለማውጣት ትልቅ መሸጋገሪያ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታመናል፡፡
ለዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፋቸውን በተለያየ መንገድ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ።
በሳምንቱ መጀመሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሩ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጫና እየደረሰባት መሆኑ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው።
ይህን ጫና ለመቀነስና ለመቋቋም የዲያስፖራው ማህበረሰብ ጠንካራ የሆነ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን የዜግነት ድርሻውን እየተወጠ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዲያስፖራው ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን መብት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግና በሌሎችም መንገዶች እየተጋለ ይገኛል።
ሰሞኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የመከረው የፀጥታው ምክር ቤት ድርድሩ የሶስቱን አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በማክበር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል መደገፉን አስታውቋል።
የዲያስፖራ ማህበረሰቡ ከዲፕሎማሲ ስራው ባሻገር ቦንድ በመግዛትና ገንዘብ በመስጠት ጭምር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለውን ድጋፍ እንደቀጠል ገልጸዋል።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።