ህብረቱ ምርጫው ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረቱ ምርጫው ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ለምርጫ ህብረት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ የምርጫ ውጤትን ይፋ የሚያደርግበትን መረሃ ግብር በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
የምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው ምርጫ የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።
በምርጫው 46 የአገር ውስጥ ሲቪክ ማህበራት ታዛቢዎች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ እንዲሁም 169 የሲቪክ ማህበራት ደግሞ ለመራጮች ትምህርት በመስጠት ለዜጎች ከፍተኛ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ለምርጫ ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ከበደ እንደተናገሩት፤ ህብረቱ በምርጫ የዜጎችን ተሳትፎ ለማበረታታት፣ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ገለልተኛና ነጻ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ህብረቱ ትኩረቱን ትዝብት እና ሚድያ ሞኒተሪንግ ላይ አድርጎ ሲሰራ እንደቆየም ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም የመራጮች ግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎች መከናወኑን ገልጸው፤ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም 800 የሚጠጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራቱንም ጠቁመዋል።
የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀምም 18 ሚልዮን ለሚሆኑ ዜጎች መድረስ መቻሉንም አመልክተዋል።
በተለይ በድምጽ መስጫ ቀን ህብረቱ 4000 ታዛቢዎችን ለማሰማራት አቅዶ 2400 ቋሚና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን ማሰማራት መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደትም ያስተዋላቸውን የትዝብት ውጤቶችን ለምርጫ ቦርድ፣ ለመገናኛ ብዙሀን እና በህብረቱ ድረ ገጽ ማሳወቁን ገልጸዋል።
በድህረ ምርጫም 110 የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን በማሰልጠን ሂደቱን በመታዘብ ላይ እንደሚገኝ አቶ ታምራት ተናግረዋል።
ህብረቱ በቀጣይ አጠቃላይ ሪፖርቱን እንደሚያቀርብ የጠቆሙት አቶ ታምራት፤በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።
ህብረቱ በቀጣይ ጳጉሜን አንድ የሚካሄደውን ምርጫ እንደሚታዘብም አስታውቀዋል።