"ቦርዱ የምርጫ ሂደቱን በገለልተኝነት ለማከናወን የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው፤ ሂደቱም የተሻለ አሳታፊ ነበር" - እጩ ተወዳዳሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
"ቦርዱ የምርጫ ሂደቱን በገለልተኝነት ለማከናወን የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው፤ ሂደቱም የተሻለ አሳታፊ ነበር" - እጩ ተወዳዳሪዎች
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን በምርጫው በእጩነት የተወዳደሩ ፖለቲከኞች ገለጹ።
ምርጫው ካለፉት አምስት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ አሳታፊ እንደነበርም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤት ይፋ ማድርጊያ መርሃ ግብር እይተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ በግልና የፖለቲካ ፓርቲ ወክለው በምርጫው በእጩነት የተሳተፉ ግለሰቦች ምርጫን በሚመለከት ያላቸውን ልምድ አቅርበዋል።
የግል ተወዳዳሪ አቶ አለሳ ተሾመ ባለፉት ሰለሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ነጻ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚህ አንጻር ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ትምህርት የተወሰደበትና የቦርዱ ገለልተኝነትም የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል።
ከምርጫ ሕግና የቦርዱ አባላት አሰያየም ጀምሮ ያሉ በርካታ ጉዳዮች አሳታፊ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ምርጫው የአሸናፊ ተሸናፊ የዜሮ ድምር ባህልን መለወጥ የሚያስችል እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አገራዊ ህልውናዋ ተጠብቆ እንዲቀጥል አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲን ወክለው በእጩነት የቀረቡት ኢንጀነር አይሻ መሃመድና ወይዘሮ ጸጋነሽ ጋመቶ በበኩላቸው፤ በምርጫው ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ ማሸነፍ እንደምትችል ያሳየችበት መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታላላቅ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው፤ ለዚህም የቦርዱን ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን አድንቀዋል።
ሰብሳቢዋ ያከናወኑት ተግባር የኢትዮጵያ ሴቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተሻለ መልኩ ማከናወን እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በግል እጩነት የተወዳደሩት አቶ ብሩክ ይላቅና አቶ ገለሳ ዴሌቦ ምርጫው የዴሞክራሲ መሰረት የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች መንግስት "ምርጫ የሚመስል ድራማ ሲያካሄድ ቆይቷል" ሲሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።