ቀጥታ፡

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መምሕራን የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር ታቅዷል - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መምህራን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ማቀዱን ማህበሩ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በማህበርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የቦንድ ግዥ እንዲካሔድ በመስራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን በተጠናከረ መልኩ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው።

ለአብነትም በተጠናቀቀው ሳምንት የ250 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽሟል።

ማህበሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዳቸው ትክክል ያለመሆኑን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።  

የሶስትዮሽ ውይይቱ "በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መቀጠል ይኖርበታል" የሚል እምነት እንዳለው መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት መርህን አክብሮ የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል አጽንኦት በመስጠት ማህበሩ መጠየቁ ይታወሳል።

በዚህ መርህም መሰረት አሁንም የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሊቋጭ እንደሚገባው የጠየቀው ማህበሩ፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የሚደረግን ጣልቃ ገብነትን ተቃውሟል።

በአረብ ሊግና ሌሎች የውጭ ሃይሎች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶች ተገቢ ያልሆኑና ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑንም በመግለጫው ጠቅሷል።

የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ያደረገው ስብሰባ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲያልቅ ድጋፍ አድርጓል።

ይህ ማህበሩ ከያዘው አቋም ጋር የሚሄድና "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" መሆን እንደሚገባው ማሳየቱን ነው የተጠቆመው።

ዶክተር ዮሀንስ እንደሚሉት፤ በአዲሱ በጀት ዓመትም የትምህርት ማህበረሰብ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽምና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ታቅደዋል።  

በአሁኑ ወቅት ከመምህራን ባሻገርም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ሀብትና ላብ የጀመረው ግንባታ እንዲጠናቀቅ ለማገዝ ሰፊ ተነሳሽነት እየታየ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም መንግስት ይሕንን እድል በመጠቀም ሃብት የማሰባሰብ ስራውን በተደራጀ መንገድ መቀጠል አለበት ያሉት ዶክተር ዩሐንስ፤ ለሕብረተሰቡም መረጃዎችን በወቅቱ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የሃይል ፍላጎት በማሟላት በኩል በርካታ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተጠቆመው።

በአለም አቀፍ ደረጃም አሁን እየተካሔዱ ያሉ የዲፕሎማሲ ስራዎችንም አጠናክሮ የመቀጠልን አስፈላጊነት አጽንኦ የሰጡት ዶክተር ዮሀንሰ፤ የተፋሰሱ አገሮች ከታላቁ ህዳሴ ግንባታ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳወቅ ረገድ ሰፊ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በተደራጀ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ማስታወቁን ኢዜአ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም