ቀጥታ፡

የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት መሆኑን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 3/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ የጠንካራ ሀገራዊ ዲፕሎማሲና የዜጎች አንድነት ተጋድሎ ውጤት መሆኑን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ ውሳኔው ዜጎች ያላቸውን የፖለቲካ ልዩነት በማክበር ለሀገር ልማትና ብሔራዊ ጥቅሞች በጋራ የመቆምን ባህል እንዲያፀኑ ያደርጋል፡፡

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ላሊ ደበሌ በሰጡት አስተያየት፤ ውሳኔው ያልተጠበቀ ግን እውነትና ኢትዮጵያ ያነገበችው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለአለም አደባባይ የተገለፀበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተገኘው ድል የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ውጤት በመሆኑ የኢትዮጵያን ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምር ታላቅ የፖለቲካ ድል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ውሳኔው የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር መደላደል የሚፈጥርና መንግስትም ተጨማሪ ብሔራዊ አጀንዳዎችን ወደፊት በማምጣት የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በውጭና ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ እያሳዩ የሚገኙትን ውትወታና አንድነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታና ልማት ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን የምታረጋግጠው የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን በማይጓዳ መንገድ መሆኑን ለአለም ማህበረሰብ ጭምር መብራራቱን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት መምህር አብይ ደምሴ ናቸው፡፡

ይህንን የመልማት ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት ለውይይት አጀንዳ አድርጎ የሚሰበሰብበት ምንም አለም አቀፍ የህግ መሠረት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በዚህ እውነተኛ ተደራዳሪዎቻችን በአጽንኦት በማስረዳት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረትና በራሳቸው በአፍሪካዎቹ እንዲፈታ መወሰኑ የሚያስደስት ቢሆንም የተገኘውን ድል ለማስፋት የተጀመረውን የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ለውሳኔው መገኘት የማህበራዊ ተስስር ገፆች፣ በአለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትም አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አብይ ገለጻ ፤የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የኢትዮጵያንና የህዝቧን ከፍታ ያረጋግጣል፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ያልተገቡ ተፅዕኖዎችን ያስቀራል፣ የቀጠናው ጂኦ ፖለቲካ ትርጉም ባለው መንገድ ይቀይረዋል፡፡

"በአጠቃላይ በአለም አቀፍም ሆነ በሀገር ደረጃ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ውጤት እንድታገኝ መንግስት በተገቢው ቦታ ተገቢውን ሰው ማስቀመጥና ማሰራት አለበት" ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአይቲ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ተሸመ ከበደ በበኩላቸው፤ የተገኘው ድል መላው ኢትዮጵያዊያንን ያኮራና ያስደሰተ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ድል የበለጠ እንዲጎመራ ሁሉም ዜጋ በእውቀት፣ ገንዘብና ቁሶች ለግድቡ የምናደርገውን አስተዋጽኦ እንደ አዲስ ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም