ቀጥታ፡

ውሳኔው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ሃብታቸው ማደግ ለሚፈልጉ ታዳጊ ሀገራት ጭምር ታላቅ ድል መሆኑን ምሁራን ተናገሩ

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 03/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያን መብት ያስከበረ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሃብታቸውን አልምተው ማደግ ለሚፈልጉ ታዳጊ ሀገራት ጭምር ታላቅ ድል መሆኑን የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።


በዩኒቨርሲቲው የውሃ ፖለቲካና የውጭ ግንኙነት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ውሂበ እግዚአብሄር ፈረደ በሰጡት አስተያየት በህዳሴ ግድብ የፍትሃዊነትና ምክንያታዊነት አጠቃቀም መርህ የተገኘው ድል ለሌሎችም ውጫዊ ጫናዎች የማንበገር መሆናችን ያረጋገጥንበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

“የአባይ ፖለቲካ የችግር ለዘመናት አእምሯችን፣ እግራችንና እጃችን አስሮ አስቀምጦን ኖሯል፤ አሁን ላይ በህዳሴ ግድብ ምክንያት የችግር ሰንሰለቱን በጣጥሰን የጣልንበት አድርጌ እወስደዋለሁ” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የዲፕሎማሲ ድሉ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ኋላ ቀርነትን ለመፍታት እንዲሁም ተራማጅ ማህበረሰብ በመፍጠር የኢትዮጵያ የማደግና የመበልጸግ ተስፋን ያለመለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ውሳኔው ግብጽ ስትጠቀምባቸው የነበሩት ኋላ ቀር አካሄዶች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዋጋ ቢስ መሆናቸውን በመገንዘብ አዲስ የትብብርና ለቀጠናዊ ትስስር የሚበጅ ሃሳብ ማምጣት እንደሚያስፈልጋት አመልክተዋል።

“በአንጻሩ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በአዲስ አእምሯዊ አቅም፣ የዲፕሎማሲያዊ ክህሎትና አስተሳሰብ የመንቀሳቀስ ሂደት ውጤት እያመጣ መሆኑን እያረጋገጥን ነው” ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያ የመደራደር አቅም እየጨመረ መምጣት የራሷን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የመጠቀም እንቅስቃሴዋ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገሩ ማረጋገጫ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን የወከሉት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት ሃሳብም በምክር ቤቱ ስብሰባ የተሳተፉ አካላትን ብዥታ ያጸዳና የተባበሩት መንግስታትን ኃላፊነት እንዳሳየ ምሁሩ መስክረዋል።

በዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዘውዱ መንገሻ በበኩላቸው፤ ግብጽ ግድቡን ከራሷ ቀደምት ግድቦችና በቅኝ ግዛት ከተደረጉ ስምምነቶች ጋር በማያያዝ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ ኢትዮጵያን ብቻ ያስከበረ ሳይሆን የሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የመልማት ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊ አገሮች ጥያቄ አያይዞ መመለሱን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የፍትሃዊነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሃሳብ በምክር ቤቱ ቅቡልነት ማግኘቱ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን በማመን ለበለጠ ስራ መነሳሳት የኢትዮጵያውያን ተግባር ነው ብለዋል።

“ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ መደረጉ ትክክለኛና ተገቢነት አለው” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዘውዱ፣ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ካረጋገጡ ማግስት ጀምሮ የቅኝ ግዛት የድንበር ውሎች እንዲከበር ያደረገ ድርጅት መሆኑን አውስተዋል።

በዚህም በድንበር ይገባኛል ምክንያት ሀገራት ወደ ግጭት እንዳይገቡ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንደ ግብጽ ያሉ አገራት መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።

አሁን ላይም በአፍሪካ ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል መርህ በብዙ ሀገራት ሰላም አስከባሪዎችን አሰማርቶ ችግሮችን እየፈታ መሆኑን ምሁሩ አስታውሰዋል።

ሱዳንና ግብጽ እውነትንና ፍትህን መሰረት ያደረገ ትብብርና ህብረት ካሳዩ በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረውን ውዝግብ በሰለጠነ አግባብ የመፍታት ሙሉ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብም በገንዘቡ፣ እውቀቱና ጉልበቱ ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ በማድረግ በዲፕሎማሲው እየተገኘ ያለውን ድል የግድቡን ፍጻሜ ዳር በማድረስ እንዲደግመው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም