የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ "ያገባኛል" መርሃ-ግብርን በይፋ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ "ያገባኛል" መርሃ-ግብርን በይፋ አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 3/2013 (ኢዜአ) የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ "ያገባኛል" የተሰኘና የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት ላይ የሚሰራ መርሃ-ግብር በይፋ አስጀመረ።
በመርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጤና ሚኒስት ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዩሃንስ ጫላን እንዲሁም ሌሎች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
መርሃ ግበሩ በዋናነት "አሰራሮችን ማሻሻል፣ ርህራሄ የተላበሰ አገልግሎት መስጠት፣ ተደራሽ መሆን፣ የአሰራር ለውጥ መተግበር እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራርን ማዳበር" በሚሉ ማእቀፎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ ሆስፒታሎች የሚተገበር ነው።
ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት መርሃ-ግብሩ በሆስፒታሎች የተሻለ እርካታን የሚፈጥር አሰራርን ለመዘርጋት ያግዛል።
መርሃ ግበሩን በተመረጡ 24 ሆስፒታሎች ለመተግባር እቅድ በማዘጋጀት የማሻሻያ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አንስተዋል።
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ መርሃ-ግብሩን በመጀር ቀዳሚ ሆስፒታል መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ሆስፒታሉ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ቀደም ብሎ መጀመሩን አንስተው፤ ይህንን አሰራር ከ"ያገባኛል" መርሃ-ግብር ጋር በማቀናጀት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ የተጀመረው በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ አሰራር ቀልጣፋ አገልግሎትን በመስጠት ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በኮሌጁ የህክምና አገልግሎት ጥራት ዳይሬክተር ዶክተር በረከት ዘላለም በበኩላቸው በሆስፒታሉ በመርሃ ግበሩ አማካኝነት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ርህራሄ የተላበሰ አገልግሎትና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በመርሃ-ግብሩ የተካተቱ እቅዶች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚተገበሩም አስረድተዋል።
ኮሌጁ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ወረቀት አልባ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውሰው፤ይህም የመርሃ ግብሩ አተገባበር ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የመርሃ-ግብሩ መጀመር በማስመልከትም በኮሌጁ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ ተከናውኗል።