ቀጥታ፡

ለበለጠ ርብርብ የሚያተጋ ተጠባቂ ውሳኔ

በሞኒተሪንግ ክፍል(ኢዜአ)

ኢትዮጵያ ያለባትን የኤልክትሪክ ሀይል እጥረት መቅረፍ የሚያስችላትን ትልቁን የሀይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ከጀመረች አስር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ወንዙን ለሚጋሩ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗን በተግባር እየገለጸች እዚህ ደርሳለች፡፡ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እ.ኤ.አ በ2015 በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት መሰረት በቅርቡ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስራው ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ለሀገራቱ በደብዳቤ ማሳወቋ ይታወሳል፡፡

የህዳሴው ግድብ ድርድርን በተመለከተ ሶስተኛ አካል ጣልቃ እንዲገባ ለዓመታት ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት ግብጽ እና ሱዳን እስካሁን ያደረጓቸው ጥረቶች በመሉ መና ቀርቶባቸዋል። ሁለቱ ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ መልኩ ጥምረት በመፍጠር በኢትዮጵያ ላይ ሴራ ሲሸርቡም ከርመዋል። የህዳሴው ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሲቃረብ ደግሞ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ሀገራቱ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተከትሎ ምክር ቤቱ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ስብሰባ አካሂዷል። ከስብሰባው ቀደም ብሎ የምክር ቤቱ የወቅቱ ፕሬዚደንት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ደ ሪቪየር ድርድሩን ወደ አፍሪካ ህብረት ከመመለስ በስተቀር በጉዳዩ ላይ ግብጽና ሱዳንን በተለየ የሚጠቅም ውሳኔም ይሁን ሃሳብ ሊቀርብ እንደማይችል ከሳምንት በፊት አመልክተው ነበር።

መቀመጫውን በግብጽ ካይሮ ያደረገው የአረብ ሊግ በግብጻዊው ዋና ጸሃፊ አህመድ አቡውል ጌይት አርቃቂነት፤ የሊጉ አባልና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተለዋጭ መቀመጫ ባላት አፍሪካዊት ሃገር ቱኒዝያ አቅራቢነት ከሁለተኛው የውሃ ሙሌት በኋላ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ድርድር ማድረግ የሚያስችል አሳሪ የስምምነት ረቂቅ ሰነድ በማዘጋጀት ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረቡ ቢሆንም ማንም ትኩረት አልሰጠውም። 

በመድረኩ ላይ የሶስቱም ሀገራት ሚኒስትሮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ “ቀደም ባሉት ጊዜያት በተደረጉት ድርድሮች ውስጥ መስማማት ባለመቻላችን አስፈላጊ የሚለውን እርምጃዎች ሁሉ በመውሰድ ውጤታማ ድርድር እንድናደርግና የጋራ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ምክር ቤቱ ያግዘናል ብለን በማመን መጥተናል” ሲሉ ተናገሩ። የሱዳኗ አቻቸው መሪየም አልማህዲም “የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በዝምታ ካለፈው ኢትዮጵያ ግድቡን በተናጠል እንድትሞላ ተስማምቷል ማለት ነው” ሲሉ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያን ወክለው በጉዳዩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሲለሺ በቀለ ንግግራቸውን የጀመሩት የምክር ቤቱን ሀላፊነት በማስታወስ ነበር፡፡ በዚህም የኤሌክሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ስብሰባ መጠራቱ የምክር ቤቱን ውድ ጊዜ ማባከን ነው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን ገልጸው፤ በምክር ቤቱ ታሪክ በመድረኩ ላይ የተገኙ ብቸኛው የውሃ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችሉም አብራርተዋል። ምክር ቤቱ የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮችን ብቻ እንዲያይና መፍትሔ እንዲሰጥ የተመሰረተ መሆኑን በመግለጽ የውሃ ጉዳይ ላይ ለመምከር ስብሰባ መጠራቱ በራሱ ትክክል እንዳልሆነ ኢትዮጵያ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ በመውጣት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የተመለከቱ ውዝግቦችን ለማየት የሚነሳ ከሆነ በርካታ ሃገራት ተመሳሳይ ጉዳዮችን ይዘው መምጣታቸው የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱም ሀገራት በወንዙ ላይ አነስተኛ እና ትላልቅ ግድቦች ገንብተው እያለ ኢትዮጵያ ባልፈረመቻቸው የቆዩ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ፤ ለተፋሰሱ የምታበረክተውን የውሃ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ባለማስገባት በውሃ ሀብቷ እንዳትጠቀም ሲከለክሉ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ “ግድቡ በኢትዮጵያውያን ላብና ደም እየተገነባ ያለ መሆኑን ዓለም እንዲያውቅልን እንፈልጋለን” በማለት “ጉዳዩ የአፍሪካ በመሆኑ መፍትሄውም በአፍሪካ ነው” በማለት የኢትዮጵያን አቋም አስረድተዋል። የጸጥታው ምክር ቤት አባላትም የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ወስኗል።

የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የአየርላንድ፣ የእንግሊዝ፣ የሜክሲኮ፣ የህንድና የኬንያ ተወካዮች ድርድሩ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ባከበረ መልኩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ግሪንፊልድ ለጉዳዩ ትክክለኛ እልባት ሊሰጥ የሚችለው አካል የአፍሪካ ህብረት ብቻ ስለመሆኑ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። ሩሲያም በበኩሏ ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ድርድሩን ማድረጉ የሚፈለገውን መፍትሄ ያስገኛል ብላ እንደማታምን በአምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዝያም በኩል ገልጻለች። አምባሳደሩ በንግግራቸውም ግጭትን የሚቀሰቅሱና ሃይል የመጠቀምን አማራጭ የሚያበረታቱ ንግግሮች አሳሳቢና በፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው” በማለት ነበር የገለጹት።

የቪየትናም ተወካይ ዳንግ ዲንህ ኩይ በበኩላቸው የአፍሪካ ህብረት ሲያደረጋቸው የነበሩ ድርድሮችን ሊቀጥሉ እንደሚገባና ሃገራቱም ሰላማዊ መፍትሄ መፈለግ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። በተመሳሳይ ቻይናን ወክለው በስብሰባው የታደሙት ዥሀንግ ጁን የአፍሪካ ህብረት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ እንደሚያስመሰግነው ገልጸው፤ ሶስቱ ሀገራት የችግር መፍቻ የውይይት ዘዴዎች መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።  

የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ በሚመለከት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከተመለከተ በኋላ ኢትዮጵያ ስታራምደው የነበረው አቋም ትክክል እና አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ ሶስቱ ሀገራት ድርድራቸውን በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲያደርጉ ምክረ-ሀሳብ ሰጥቶ መበተኑ ኢትዮጵያ ይዛው ከነበረው የማያወላውል ጽኑ አቋም አንጻር ውጤት ያስገኘ ነው።የጸጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ጭምር ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ድሉ ሙሉ የሚሆነውና ህዝቡም ሊኮራ የሚችለው የግድቡ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በመሆኑ የአሁኑን ድል እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያለ ዜጋ  አሁንም ቀደም ሲል ሲያደርግ እንደነበረው በአንድነት በመቆምና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለዋናው ድል እንዲበቃ መረባረብ ይኖርበታል፡፡ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም