ቀጥታ፡

በመተከል ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 3/2013(ኢዜአ) በመተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ኮማንድ ፖስት ገለጸ።

በመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረኃይል ኮማንድ ፖስት የተመራ ልዑክ ከአማራ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች፣ ከመተከል ዞንና ከየወረዳዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች በአራት የወረዳ ማዕከላት የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን ጎብኝተዋል።


ተፈናቃዮቹ በማንዱራ ወረዳ ገነተማርያም ከተማ ማዕከል፣ የድባጤ ወረዳ ድባጤ ከተማ ማዕከል፣ የቡለን ወረዳ ዶቢ ቀበሌ ማዕከል፣ የዳንጉር ወረዳ ደግሞ ማንቡክ ከተማ ማዕከል እንዲያርፍ ተደርጓል።


በጉብኝቱ ወቅት በሁሉም ማዕከላት የሚገኙ ዜጎች እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ ፍራሽ፣ አልባሳት እንዲሟሉላቸው፣ የህክምናና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲጨመርላቸው፣ ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፎች በሰዓቱ እንዲሰጣቸውና እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል።


የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ደህንነታቸውን ለመጠበቅ እያደረጉት ላለው አስተማማኝ ጥበቃም ምስጋና አቅርበዋል።


በዞንና ወረዳ ደረጃ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት እስከቀበሌ ድረስ ወርዶ ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችና መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል።


የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንደተናገሩት፤ መንግስት በዞኑ የተለያዩ የወረዳ ቀበሌዎች ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።


የዞኑ ኮማንድ ፖስቱና መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ከዞን እስከቀበሌ ድረስ እርቀ ሰላም እንዲወርድ በማድረግ ወደ የመኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።


የምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጀኔራል አለማየው ወልዴ በበኩላቸው፤ ድጋፉ ለሚመለከተው አካል እንዳይደርስ በተፈናቃይ ስም የሚያጭበረብሩ አካላትን በማጋለጥ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


በየማዕከላቱ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅም ሰራዊቱ በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ በየማዕከሉ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሙሉ ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሟላት በመጓጓዝ ሂደት ላይ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ በየማዕከላቱ እንደደረሱም በአስቸኳይ እንዲሰራጭ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።


የህክምና አገልግሎት፣ የአልባሳት፣ የድንኳን ማነስ እና ሌሎች የመገልገያ ቁሳቁሶች እጥረቶች እንደሚሟሉም በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም