የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ተመሰረተ።
ማህበሩ በአሜሪካ የአለም አቀፍ የልማት ድርጅት "ፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ" በተሰኘ ፕሮጀክት ትብብር የተመሰረተ ሲሆን፤ የምስረታ ጉባኤውንም ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዷል።
ማሕበሩ በህግ ትምህርት ቤቶች መካከል ትብብርን በማጠናከር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በጋራ መስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የማህበሩ ሊቀመንበር ዶክተር ሰለሞን ተክሌ እንዳሉት የማህበሩ መመስረት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ላይ በጋራ እንዲሰሩ ያስችላል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ትምህርት ቤቶች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንደሚያግዝም ጨምረው ገልጸዋል።
የማህበሩ አለመኖር የህግ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ተግባራትን በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱንም ነው ያነሱት።
የማህበሩ ዋነኛ አላማ የህግ ትምህርት ቤቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ነጻ የመወያያ መድረክ ሆኖ ማገልገል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የህግ አማካሪና አቃቢ ህግ ቴድሮስ ምህረቴ ናቸው።
በህግ ትምህርት ቤቶች መካከል ትብብር መፍጠር፣ ሃብት ማሰባሰብና መጋራት፣ የህግ ትምህርት መስፈርት እንዲኖረውና ትምህርት ቤቶቹም ይሕንን እንዲከተሉ ማገዝ በማህበሩ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
በተጨማሪ ማህበሩ የህግ ትምህርት ቤቶች ወቅቱን ያገናዘበ ትምህርት እንዲሰጡ ማገዝ፣ ብሔራዊ የህግ ስርአተ ትምህርት ተግባራዊነትን መከታተልና ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
"የፍትህ ተግባራት በኢትዮጵያ" የፕሮጀክቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ በላይ፤ ኢትዮጵያ የህግና ፍትህ ስርዓቷን እንዲሁም የህግ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት ውስጥ የማህበሩ ሚና ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ማህበሩን በመደገፍ ረገድ ድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
ማህበሩ የህግ ትምህርትን የሚሰጡ 36 የመንግስት ከፍተኛ ትምህር ተቋማትን በአባልነት ይዟል።
በምስረታ ጉባኤውም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የህግ ትምህርት ቤት ዲኖችና ተወካዮች፣ የሲቪል ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።