ቀጥታ፡

በጅግጅጋ ከተማ የተፈጠረው አለመረጋጋት እንዲወገድ ሁሉም በፀሎት እንዲተጋ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች

አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተፈጠረውና በንፁሃን ዜጎች ላይ ከባድ ፈተና ሆኖ ጉዳት ያደረሰው ጥቃት ተወግዶ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም በፀሎት እንዲተጋ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ የሚጀመረውን የፍልሰታ ፆም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢዜአ በላከችው መግለጫ ህዝበ ክርስቲያኑ ወቅቱን ከሌሎችና የእምነቱ ተከታዮች ጋር በሰላምና በመከባበር እንዲያሳልፉ ጠይቃለች። በአገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች ቅድሚያ የሚጎዱት ህፃናት በመሆናቸው በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ህፃናትና ተጎጂዎችን ማሰብ ይጠበቅብናል ሲሉ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደተለመደው ከህዝቡ ጎን በመቆም ተጎጂዎች ባሉበት አስፈላጊውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል። በኢትዮጵያ ብሎም በመላው አፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም በአንድነት ተባብሮ መስራት አንዳለበት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል አሳስበዋል። ህዝበ ክርስቲያኑ ፆመ ፍልሰታን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በፆምና በፀሎት ማሳለፍ እንዳለበትም ቤተክርስቲኗ አስገንዝባለች። ህዝበ ክርስቲያኑ ፆመ ፍልሰታን ከእግዚአሔር ከተሰጠው ፀጋ ለድሆች በማካፈል ማሳለፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል። "እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተቸገሩትን መርዳት እንዳስተማረችን ሁሉ እኛም የድንግል ማርያምን መልካም ተራዳይነት በተግባር ማሳየት አለብን" ሲሉም ነው ካረዲናል ብርሃነየሱስ የመከሩት።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም