ቀጥታ፡

የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል - ዶክተር አረጋዊ በርሔ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፤2013 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተፋሰሱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት እንዲወያዩ ድጋፍ ማድረጉ ተገቢ መሆኑንም ተጠቁሟል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 16 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለው ተሳትፎ መጨመሩንም ነው የገለጹት።

በ2013 ዓ.ም ብቻ ዲያስፖራው ለግድቡ ግንባታ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማዋጣቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የግድቡ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሊት እየተከናወነ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ብስራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ አለባቸው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ከግድቡ ባሻገር የሀገር ጥቅምን ለማስጠበቅ በቅንጅት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያውያን በተደራጀ መንገድ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ትስስር መፍጠሩንም ጨምረው ገልፀዋል።

ግብጽና ሱዳን ለአለማቀፉ ማሕበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያ ተገቢ ድጋፍ እንዳታገኝ ተጽእኖ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት፣ በዲፕሎማቶችና ዳያስፖራዎች ይህን ተጽእኖ ለመመከት በርካታ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የፀጥታው ምክር ቤት የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲሆን ድጋፍ ለማድረጉ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ነው ያመለከቱት።

የፀጥታው ምክር ቤት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ያሳየው ድጋፍ ዲፕሎማሲያዊ ድል መሆኑንም ዶክተር አረጋዊ ተናግረዋል።

የግድቡ ውሃ ሙሊት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በ2015 የደረሱበትን የስምምነት መርሆች ባከበረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ትናንት በተካሔደው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የውሃና መስኖ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ "የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ደም፣ ላብና እንባ የሚገነባ ነው" ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም