የምክር ቤቱ ውሳኔ ግብፅና ሱዳን ተባብሮ መስራት መርህ ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱ ውሳኔ ግብፅና ሱዳን ተባብሮ መስራት መርህ ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ
ሀዋሳ ሐምሌ 2/2013 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሕዳሴው ግድብ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል መወሰኑ ግብፅና ሱዳንን ተባብሮ መስራት መርህ ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደተናገሩት፤ ውሳኔው ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በአፍሪካ ደረጃ የሚፈታውን ድርድር ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ማቅረባቸው ተገቢ አልነበረም።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ፈቀደ ምኑታ ምክር ቤቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሳለፈው ውሳኔ የምንጠብቀው ስለነበር ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
ውሳኔው ግብፅና ሱዳን ተባብሮ በመስራት መርህ ላይ ድርድሩን እንዲያካሂዱ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ የምታከናውነው ማንንም ለመጉዳት እንዳልሆነ ያስታወሱት ዶክተር ፈቀደ፣ ግብጽና ሱዳን አሁንም ይህንን አቋሟን በመረዳት ድርድሩን መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ዶክተር ፈቀደ ፤ ግንባታው እየተገባደደ ባለው ግድብ መተሳሰብ እንጂ፤ አምባጓሮ መፍጠርና በጥላቻ መንገድ መንቀሳቀስ ለማንም እንደማይበጅ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ የተጀመረው ህዝባዊ መነቃቃትና ድጋፍ መቀጠል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ኢንጂነር በላቸው ያዕቆብ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ሁለቱ ሀገራት የግድቡን ጉዳይ የጸጥታ ጉዳይ አስመስለው ያቀረቡትን አጀንዳ ወደ አፍሪካ መድረክ መመለሱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ማስረጃም ልብ የሚነካ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል መወሰኑ ግብጽና ሱዳን የሚያዋጣቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት መሆኑን አሳይቷል ሲሉም አመላክተዋል።
ይህም ሶስቱንም ሀገራት አሸናፊ እንደሚያደርጋቸው ገልጸው፤ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በወንድማማችነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ደምሰው ባቾሬ ፤ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና ዓለም አቀፍ ህግን መሠረት በማድረግ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ገልጸዋል።
ይህ እንቅስቃሴዋ ያልተዋጠላቸው ግብጽና ሱዳን ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥሉ መወሰኑ የኢትዮጵያን ትክክለኛነት ለዓለም ህዝብ በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።
አስተያየት ሰጪው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2015 ካርቱም ላይ የተፈራረሙት "የመርሆዎች ስምምነት" የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ አጠቃቀም ለመምራት ያስቻላል፤ ስምምነቱ የግድቡን የውሃ ሙሌትም ያካትታል።
ሆኖም ግብፅና ሱዳን ከስምምነቱ በማፈንገጥ በየጊዜው በሚያነሷቸው አጀንዳዎች ችግር ሲፈጥሩ እንደሚስተዋል አስታውሰው፤ ጉዳዩንም ሌሎች አካላት ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር እንዲያስፈጽሙላቸው ሲጥሩ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።
ውሳኔው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካ መፍትሄ ለመስጠት የምታራምደውን አቋም ትክክለኝነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የምትከተለው ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግድብ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ቀደም ብሎ ተገልጿል።