የሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማቀናጀት ለስራ እድል ፈጣራ መጠቀም ይገባል ... የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማቀናጀት ለስራ እድል ፈጣራ መጠቀም ይገባል ... የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2/2013(ኢዜአ) የሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማቀናጀት ለስራ እድል ፈጣራ መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ገለጸ።
አካዳሚው "የሰው ሃብት ግንባታ ለስነ ህዝብ መሳካት" በሚል መርህ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት አካዳሚው የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን እያቀረበ ነው።
የሰው ሀብት ግንባታና የኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ትስስር በማጠናከር አገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
እንደ ኮሪያ ያሉ "የኤዥያ ታይገርስ" የሚባሉ ሀገራት የሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊው በማቀናጀት ስራ ፈጣሪ ዜጎችን መፍጠር እንደቻሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ያሏትን የአገር በቀል እውቀቶች በተገቢው ሁኔታ መጠቀም አለባት ብለዋል።
የሀገር በቀል እውቀቶች ከዘመናዊ ጋር ተቀናጅተው በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ መተግበር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት
ትምህርትና ስልጠና ለኢኮኖሚ ፣ለማህበራዊና ለፖለቲካዊ እድገት እንዲሁም ለስራ ፈጠራ መነሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት እርከን የተግባር ትምህርት በመስጠት የፈጠራ ክህሎት ባለቤት በማድረግ ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የገለጹት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕቅድና ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ቀነኒሳ ዳቢ በበኩላቸው ጥራት ያለውና በተግባር የተደገፈ ትምህርት አምራች ዜጎችን በማፈራት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶችን የያዘች ሀገር መሆኗ ደግሞ አምራች ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ እድል እንዳለውም አንስተዋል፡፡
ወጣቱ በልማት እንዲሳተፍና ውጤታማ እንዲሆን አገሪቷ የምትከተለውን የልማት አቅጣጫ ያገናዘበ ስርዓተ ትምህርት መዘርጋት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡