ቀጥታ፡

ፀጥታው ምክር ቤት ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን እንዲፈታ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ ነው -ምሁራን

አዳማ ፣ሐምሌ 02/2013-(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን እንዲፈታ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢና የሚደነቅ መሆኑን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምሁራን አስታወቁ።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷንና ፍትሃዊ የውሀ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ መርህን መሰረት አድርጋ ከድህነት ለመላቀቅ እያካሄደች ያለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መወሰዱ ቀድሞውኑ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ምሁራኑ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የፊዚክስ መምህርና የቅድመ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ሰለሞን ጥሩነህ እንደገለጹት የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን እንዲፈታ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢና የሚደነቅ እርምጃ ነው።

"ኢትዮጵያ በታሪክ ሌሎች ሀገሮችን ጎድታ አታውቅም" ያሉት ዶክተር ሰለሞን ኢትዮጵያ በቅርቡ ሱዳን የገባችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ የፈታችበትን አግባብና ኮሪያን ያገዘችበትን ተግባር ለአብነት ጠቅሰዋል።

የህዳሴ ግድብ  ግንባታ  ዓላማ ልማትና እድገት ብቻ መሆኑ እየታወቀ ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የተወሰደበት አግባብ  ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ምክር ቤቱ ትክክለኛውን የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ፍላጎት እንዲገነዘብ፣ የግድቡ ዓላማ ከድህነት፣ ኋላቀርነትና ድንቁርና ለመውጣት ያለመ መሆኑን በምሳሌ ጭምር በማስረዳት ያሳመኑት የኢትዮጵያ ልዑካን የሚመሰገኑና ሉዓላዊነታችን ጭምር ያስጠበቁ ናቸው" በማለት አድናቆታቸውን ችረዋል።

"ግድቡ በፍጥነት ተጠናቆ  ኢትዮጵያ  የያዘችው አፍሪካዊ ራዕይ እውን እንዲሆንና ቀጠናዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲፋጠን ባለን ሁሉ ማገዝና ልማቱን መደገፍ አለብን" ብለዋል።

ግብፅና ሱዳን የግድቡ ግንባታ የሚጎዳቸው ሳይሆን የጋራ ልማትና አብሮ ማደግን የሚያረጋግጥ በመሆኑ በአፍሪካዊያን ላይ የተጫነው የኢኮኖሚና የህልውና እጅ አዙር አገዛዝ  እንዲያበቃ በትብብር ለመስራት ህዝባቸውን ጭምር ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል" ሲሉም አመልክተዋል።

"በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ዜጎች ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል" ያሉት ዶክተር ሰለሞን "ሃያላን ሀገራት የሚፈጥሩትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በአንድነት ተቋቁመን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ ይገባናል" ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ መምህርና የልህቀት ማዕከል ዲን ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ በበኩላቸው "የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ምሁራን፣ መላው ህዝብና መንግስት በአንድነት በመቆማቸው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ተፅዕኖ የፈጠርንበት እርምጃ ነው" ብለዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን ጥላ ስር እንዲሆን የድርድሩን ሂደት ወደ አፍሪካ ህብረት መመለሱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስጠበቀ ውሳኔ መሆኑንም አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ ብቻ እንዲፈታ የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት ላይ የነበራቸውን ያነሰ አመለካከት የቀየረ ተግባርና እርምጃ መሆኑን ዶክተር ዓለሙ ተናግረዋል።

የአረብ ሊግን ጨምሮ ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ለማወሳሰብ የፀጥታ ጉዳይ ያልሆነውን የግድቡን ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዳቸው ያልተሳካ ሙከራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

"የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን መሆኑ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ነው" ያሉት ዶክተር ዓለሙ "የአፍሪካ ህብረት ለግብፅ፣ ለሱዳንና ለኢትዮጵያ እኩል የሚሰራና የሚወስን በመሆኑ ሀገራቱ ራሳቸውንና ህዝባቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ እንደጀመረው በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ድጋፍ በማድረግ የግድቡ ግንባታ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ሀላፊነቱን መወጣት አለበት" ያሉት ዶክተር ዓለሙ መንግስት ዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ በትኩረት መስራትን ሊቀጥልበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም