ቀጥታ፡

በምዕራባዊያን የሚተላለፉት መግለጫዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የጣሱ ናቸው... ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2013(ኢዜአ)በምዕራባዊያን በኩል የሚተላለፉ መግለጫዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን ጣልቃ ገብነት መሆኑን የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።

የህገ መንግስትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ የኢትዮጵያን መንግስት እንጂ "የትኛውንም የውጭ ሀገር አይመለከትም" ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚያወጡት መግለጫዎች ትክክለኛውንና ተጨባጩን የአገሪቷን ሁኔታ ያላገናዘቡ፣ ለአንድ ወገን ያደሉ፣ በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ፣ ሉዓላዊነትን የሚዳፈሩ መሆናቸው የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ።

የአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ህዳር 05 ቀን 2020 ባወጣው መግለጫ "ኢትዮጵያ ህገ መንግስቷን፣ የውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኗንና የውጭ ድንበሯን መለወጥ አትችልም" ሲል ያወጣው መግለጫን ምሁራኑ ለአብነት ያነሳሉ።

በቅርቡ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ "ኢትዮጵያ ህገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ የውስጥም ሆነ የውጭ ድንበሯን ፈጽሞ መለወጥ አትችልም" ሲሉ የተናገሩትን ሌላው ማሳያ ነጥብ አድርገው ይጠቅሱታል።

የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የምዕራባዊያኑ መግለጫዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር የሚጋፋ ብሎም የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህን የተላለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በህወሓት የሽብር ቡድን የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ህግ የማስከበር ዘመቻ በምታከናውንበት ወቅት ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጡ እንደነበርም አስታውሰዋል።

አብዛኛውቹ አስተያየቶች መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የካዱና በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ  መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተለይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል የሚወጡ ተደጋጋሚ መግለጫዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፉ፣ ዓለም አቀፍ የግንኙነት የተላለፉ ግልጽ ጣልቃ ገብነቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ "መብረቃዊ" ያለውን ጥቃት ሲፈጽም በማይካድራ ንጹሃንን በማንነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድል አሜሪካ "ጉዳዩን እንዳላየች ሆና አልፋዋለች" ብለዋል።

በተጨማሪ አሜሪካ በተለያዩ አከባቢዎች በኢትዮጵያ የተከሰቱ ሰብዓዊ ቀውሶች ላይ ምንም አስተያየት አልሰጠችም፤ የመደገፍ ሙከራም አላደረገችም ነው ያሉት።

ነገር ግን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ ጥቃት ባደረሰ ወንጀለኛ ቡድን ላይ ህግ ማስከበር ሲጀመር "ለምን" የሚል ወገንተኝነት ያለው ጥያቄ ይዛ መነሳቷን ገልጸዋል።

"የህወሃትና አሜሪካ ጋብቻ" የቆየ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ አሸባሪው ህወሃት ደርግን ለመጣል የትጥቅ ትግል በሚያከናውንበት ወቅት አሜሪካ በእርዳታ ስም የተለያዩ ድጋፎችን ታደርግለት እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቀናት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ይህንኑ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አንጸባርቀዋል።

ይሁን እንጂ ህገ መንግስቱን የማስከበርና የአስተዳደር ወሰንን የመከለል ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እንጂ የአሜሪካ ስልጣን እንዳልሆነም አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍም በአሜሪካ ግፊትና ውትወታ ወይም ማስፈራሪያ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎትና ኃላፊነት የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።

"አሜሪካ ጣልቃ የገባችባቸው እንደ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያና መሰል አገራት ሲፈራርሱ እንጂ ዲሞክራሲ ሲሰፍንባቸው አላየንም" ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ተናግረዋል።  

ሌላው የአሜሪካ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መነሻው ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛች ነፃ ሀገር በመሆኗ ከአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር መወዳጀቷ ሊሆን እንደሚችልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሜሪካ ከመፈጠሯ በፊት የነበረች ታላቅ አገር በመሆኗ ለእድገቷና ሉዓላዊነቷ ከሚመጥኗት አገራት ጋር መርጣ መወዳጀት እንደምትችልም አብራርተዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድንን ተጠቅመው ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር ይህንን የኢትዮጵያን መብት ለመጣስ እየሞከሩ መሆኑንም አውስተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከተቋም ይልቅ የግለሰቦችን ሀሳብ እያንጸባረቀ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ በአሜሪካ ጫና የትኛውንም አይነት ውሳኔ መቀየር የለባትም፤ አሜሪካ እንደጸጥታው ምክር ቤት ትክክለኛ አቋም እስከምታራምድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ አለባት" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና አፍሪካውያን ላይ ተጽእኖ የሚያደርስ በመሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ጉዳዩን የራሴ በማለት አሜሪካን በቃሽ ሊሏት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም