"የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ጉዳይ ሆኗል" - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ጉዳይ ሆኗል" - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 02/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአገኘችው ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል "የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ጉዳይ ሆኗል" ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው አበይት ፖለቲካዊ ምጣኔ ሀብታዊና የዜጋ ዲፕሎማሲ ክንውኖችን አንስተዋል።
ትናንት በመንግሥታቱ የፀጥታ ምክር ቤት የቀረበው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሦስትዮሽ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ በሁሉም የምክር ቤት አባላት ዘንድ የተገኘ "ትልቅ ዲፕሎማሲ ስኬት ነው" ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ከምክር ቤቱ ስብሰባ ቀደም ብሎ ዘርፈ-ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ጉዳዩ ቀድሞውኑም ወደ "ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ አልነበረበትም" ያሉት አምባሳደሩ፤ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላትም ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ዳግም ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ላይመለስ በአፍሪካ ህብረት እንዲመራ ድጋፍ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ እንዲታይ የሚደረግ ይሆናል፤ ኢትዮጵያም የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት መሪነት እንዲቋጭ ትሻለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በኒዮርክ በሚገኘው የምክር ቤቱ መሥሪያ ቤት ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ለውሳኔው አዎንታዊ ሚና ያሳደረ አስደናቂ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
"ከዚህ በኋላ የግድቡ ውሃ ሙሌትም እስከ ሰባተኛው ዙር ይቀጥላል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ በተያዘው ክረምት ወራት ጎረቤት አገሮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ማድረጓን ገልጸዋል።
ለግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም እንዲያግዙ፣ በተለይም ለዓባይ ወንዝ ደህንነት ከተቆረቆሩ ከእምቦጭ አረም መከላከል እና ተፋስስ ልማት ላይ ድጋፍ ቢያደርጉ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከሚገኙ በናይል ተፋሰስ አገሮች አምባሳደሮች ውይይት መደረጉን አስታውሰው፤ ግድቡ የልማት አጀንዳ እንጂ የጸጥታ ጉዳይ ባለመሆኑ ሱዳንና ግብፅ የሄዱበት መንገድ አግባብነት እንደሌለው መግለጻቸውን አንስተዋል።
የድርድሩን ጉዳይ ወደማይመለከተው ፀጥታ ምክር ቤት እንዲቀርብ ያደረገው የዓረብ ሊግ ጥያቄ የአፍሪካ ህብረትን የመናቅ እና አሳንሶ የማየት ጉዳይ በመሆኑ አምባሳደሮቹ እንዳወገዙት ተናግረዋል።
በትግራይ የተደረገው የተናጠል ተኩስ አቁም አመክንዮ በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለውጭ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ገለጻ መደረጉንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረስ የሚሹ አካላት የበረራ ፈቃድ መሰጠቱን አምባሳደር ዲና ገልጸው፤ ነገር ግን በረራዎቹ በአዲስ አበባ በኩል ብቻ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
በአሸባሪው ህወሃት የፈረሰው የተከዜ ድልድይን ለመጠገን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዜጋ ዲፕሎማሲ ረገድም ባለፈው ሳምንት 21 ሺ 182 ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ መመለሳቸውን፤ ከእነዚህም መካከል 3 ሺህ 600ዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 'ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችን እየዘጋች ነው፤ ሠራተኞችንም እየጠራች ነው የሚል መረጃ አለ' በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን በተጨባጭ የዘጋችው ኤምባሲ እንደሌለ ገልጸው፤ ነገር ግን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደማንኛውም ተቋም ሪፎርም ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይ የሚቀነሱ ወይም የሚዘጉ ኤምባሲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ የሠራተኞችን ጥሪ በተመለከተም የተለመደ አሠራር መሆኑን አብራርተዋል።