ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን - ባለሃብቶችና የንግድ ማህበረሰብ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን - ባለሃብቶችና የንግድ ማህበረሰብ አባላት
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 02/2013(ኢዜአ) ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ባለሃብቶችና የንግዱ ማህበረሰቦች ገለጹ።
"ክብር ለአገራቸው አንድነት እና አብሮነት ለተሰዉ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን አባላት" በሚል ሃሳብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በመዲናዋ ከሚኖሩ ባለሃብቶችና የንግድ ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሰላምና በአብሮነት በጋራ ለመስራት፣ ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን ደጀንነትና ክብር ለማሳየት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ስራ ለማጠናከር ያለመ ነው።
በመድረኩም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበረውን ቆይታ አስመልክቶ ገለፃ ተደርጓል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት በተሰማራባቸው የጦር ግንባሮች ሁሉ ድል የሚቀዳጅ በባህሪውም ሆነ በሰብዕናው የተመሰገነ ጀግና ሠራዊት ነው።
ብዙዎች ይህን መልካም ተግባሩን ለማጉደፍና ለማጠልሸት ቢፈልጉም ሠራዊቱ ህዝባዊ በመሆኑ ሊሳካላቸው አለመቻሉን ነው የተናገሩት።
ይህ “ብሔራዊ አርማችን የሆነውን የመከላከያ ሠራዊታችን" በአብሮነት በመቆም ማጠናከር፣ ማበረታታት እና አለውልህ ማለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
"ሠራዊቱን በምንችለው አቅም በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስ በሞራል ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ በመደገፍ ሠራዊቱ አገራዊ መሰረት ያለው መሆኑ ለወዳጆቻችንም ለጠላቶቻችንም ማሳየት አለብን" ሲሉ ለባለሃብቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል የወጣበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሠራዊቱ ከአካባቢው እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ክረምት በመሆኑ አርሶ አደሩ እርሻውን እንዲያርስ እና ህዝቡ የክልሉን ሁኔታ በጥሞና እንዲመለከተው በማሰብ ነው።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለአገር ስጋት እንደማይሆን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል ባጫ፤ ሠራዊቱ በማንኛውም ሰዓትና ቀን መቀሌ መሄድና መቆጣጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል።
"የመከላከያ ሠራዊት ማጠናከር አገር ማጠናከር ነው" ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በማጠናከር ታላቅ የነበረችውን ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ከፍታ ማማ መመለስ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውታል።
ባለሃብቶቹ በበኩላቸው ለአገር ሠላም በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረው፤ ለአገር ሉዓላዊነት በየበረሃው ለሚዋደቀው የአገር መከላከያ ሠራዊት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሞራል ድጋፍ ለማደረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም አክለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የመከላከያ ሠራዊትን ለማጠናከር ከተለያዩ አካላት ሁለት ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሠራዊት 500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።