ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያሳዩትን አንድነት በሰላም ግንባታ ሊደግሙት ይገባል--የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያሳዩትን አንድነት በሰላም ግንባታ ሊደግሙት ይገባል--የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2/2013 (ኢዜአ) ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያሳዩትን አንድነት በሰላም ግንባታ ሊደግሙት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላም እና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ከተለያዩ አደረጃጀቶች እና ተቋማት ጋር በመሆን በየካ ሚሊንዬም ፓርክ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሄዷል።
የሊጉ ፕሬዝዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ በዚህ ወቅት በመርሃ-ግብሩ አንድ ሺህ 500 ችግኞች እንደተከሉ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
በመርሃ-ግብሩ የተሳተፈው ወጣት አደባቤ ካሰው ወጣቶች በአንድነት አረንጓዴ አሻራቸውን እንዳሳረፉ ሁሉ በሰላም ግንባታውም የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጿል።
በህዳሴ ግድብ ላይ የሚታዩ ጣልቃ ገብነቶችንም በአንድ ልብ ሆኖ መመከት እንደሚገባ ጠቁሞ፤ ወጣቶች ባላቸው እቅም ሁሉ ሀገራቸውን መደገፍ እንዳለባቸው ተናግሯል።
ሌላኛው ወጣት አብዱልሀቅ አህመድ በበኩሉ የሀገር ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ወጣቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጸው።
በመሆኑም ወጣቶች ለሰላምና አብሮነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል።
መልካም ነገርን በመሥራት፣ በመተባበርና በመተጋገዝ ወጣቶች እራሳቸውን እና አገራቸውን ሊቀይሩ ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት አየለ አክሊሉ ነው።
ወጣቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ ሀገራቸውን ነቅተው መጠበቅ አለባቸውም ነው ያለው።
ወጣት ዘሀራ ተካ በበኩሏ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ወጣቱን ሊያደናግሩት አይገባም ብላለች።
ወጣቶች ከታማኝ የመረጃ ምንጮች እንዲሁም በመንግሥት የሚተላለፉ መግለጫዎችን በመጠቀም ለሐሰተኛ መረጃዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።