ቀጥታ፡

የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከመገንባት የሚያስቆማት ሀይል እንደሌለ ያሳየ ነው- ምሁራን

ጅማ፣ ሀምሌ 02/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷንና ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ መርህን መሰረት በማድረግ እያካሄደች ያለውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስቆማት ሀይል እንደሌለ ያሳየ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያ የተሻለ የዲፕሎማሲ የበላይነት የተጎናጸፈችበት መሆኑንም ምሁራኑ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ መምህር ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብጽ በተናጠል አሸናፊና ተጠቃሚ ለመሆን የምትሄድበት መንገድ ተቀባይነት የለውም።

ግብጽ እካሄዷ እየጠቀማት እንዳልሆነም ጠቁመው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲታይ ያሳለፈው ውሳኔም ግብጽ በያዘችው የተናጠል ተጠቃሚነት አካሄድ እንደማትቀጥል ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ባንጻሩ ውሳኔው የኢትዮጵያን ፍትሀዊነት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።


ምክር ቤቱ በስብሰባው የደረሰበት ውሳኔ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷንና ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ መርህን መሰረት በማድረግ እያካሄደች ያለውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስቆማት ሀይል እንደሌለ ያሳየ መሆኑን ዶክተር ደመላሽ አስታውቀዋል።

"ኢትዮጵያ ህዝቦቿን ከጨለማ ለማውጣት በምታደርገው ጥረት የዓለም ማህበረሰብም ሆነ ጎረቤት ሀገራት መተባበር ሲገባቸው ይህን መሰል ጫና ማድረግ ተገቢ አልነበረም" ብለዋል፡፡


"ኢትዮጵያ በታሪክ ነፃና ሉአላዊነቷን በተባበረ የአንድነት ክንድ አስከብራ የኖረች ሀገር መሆኗን መላው ዓለም የሚረዳው እውነት ነው" ያሉት ዶክተር ደመላሽ  ድህነትን ድል ለመንሳት በምታርገው ትግልም የማንም ተጽእኖ እንዲያርፍባት አትፈልግም " ሲሉ ገልጸዋል።


ኢትዮጵያዊያን በህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው አንድና የጠነከረ አቋም ኢትዮጵያን ለተሻለ ድል የሚያበቃት መሆኑን የገለፁት ዶክተር ደመላሽ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሩ አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።


"ኢትዮጵያ የአብሮ መጠቀም መርህን በመከተል ስታካሂደው የቆየችው የድርድር ሂደትም እውነትንና ፍትህን ያስቀደመ በመሆኑ የጀመረችውን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ከቶ የሚያስቆማት ሀይል አለመኖሩን አሳይታለች’’ ብለዋል ፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር የማነብርሀን ቀለመወርቅ በበኩላቸው የጸጥታው ምክር ቤት ያካሄደው ስብሰባ አንድምታ በራሱ ጉዳዩ መቅረብ ባልነበረበት ቦታ መቅረቡ ኢ-ፍትሀዊ እንደነበር አመልክተዋል፡፡


"ኢትዮጵያ የያዘችው ፍትሀዊና የጋራ ተጠቃሚነትን የተከተለ አቋም ተጽእኖ ለመፍጠር የሚቋምጡ አካላትን መልስ ማሳጣት አስችሏታል" ብለዋል፡፡


"የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያ አቋም ጎልቶ መውጣት የቻለበት ዋነኛው ምክንያት በእውነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው" ያሉት ዶክተር የማነብርሀን በስብሰባው ኢትዮጵያ የተሻለ የዲፕሎማሲ የበላይነት የተጎናጸፈችበት መድረክ እንደነበር አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር የማነብርሀን ገለጻ ኢትዮጵያ ወደፊትም አቋሟን ያለማቋረጥ ለዓለም ማስረዳት አለባት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም