ህዳሴው ግድብ ሀይል ማመንጨት እስከሚጀምር ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን---የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ህዳሴው ግድብ ሀይል ማመንጨት እስከሚጀምር ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን---የመንግስት ሰራተኞች
ጎባ ሀምሌ 2/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባሌ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ፡፡
በዞኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ በቦንድ ግዥ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
በዞኑ ሮቤ ከተማ የቦንድ ግዥ የፈጸሙ የባሌ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ትስስር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልቺሳ ዘውዴ እንደገለጹት ለህዳሴ ግድብ በቦንድ ግዥ በተለያዩ ዙሮች በመሳተፋቸው ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ለግድቡ ግንባታ እየተደረገ ባለው የድጋፍ መርሃ ግብር የመስሪያ ቤታቸውን ሰራተኞች በማስተባበር ከ32 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን አመልክተዋል፡፡
"መንግስት የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ግድቡ በተያዘለት ጊዜ የውኃ ሙሌቱ እንዲከናወን ለማድረግ የያዘው አቋም ሀገሪቱንና ህዝቧን ከድህነት ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ተግባር ነው "ያሉት ደግሞ ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ኡመር አብደላ ናቸው፡፡
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለሚፈለገው አገልግሎት እስኪበቃ ድረስ የጀመሩትን የቦንድ ግዥ እንደሚቀጥሉበት አቶ ኡመር ተናግረዋል፡፡
"የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በእድገት ጎዳና ላይ እንድትራመድ እንደሚያስችላት በመረዳቴ ከደሞዜ ለሶስተኛ ዙር የ2ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽሜያለሁ" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሀሊማ ከድር ናቸው፡፡
"ታላቁ የህዳሴ ግድብ በእያንዳንዱ ዜጋ ወዝ የሚገነባ የኢትዮጵያዊያን ሀብት ነው "ያሉት የመንግስት ሰራተኞቹ ሁሉም ዜጋ ለግድቡ የውኃ ሙሌትም ሆነ ግንባታ መጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የዞኑ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጻኃፊ አቶ ታምሩ ጋረደው በበኩላቸው በዞኑ በ2013 በጀት ዓመት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዞኑ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተፈጸመው የቦንድ ግዥ በዓመቱ ለማከናወን በዕቅድ ከተያዘው 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ውስጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
በባሌ ዞን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከዞኑ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡