ቀጥታ፡

ምዕራባውያን "እጃችሁን አጣጥፋችሁ የምንላችሁን ብቻ አድርጉ " የሚል አካሄድ እየተከተሉ ነው - ምሁራን

ሀምሌ 1/2013 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊያን በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ የሚሞከሩት ተጽእኖ "እጃችሁን አጣጥፋችሁ እኛ የምንላችሁን ብቻ አድርጉ" ከሚል የሚመነጭና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ድርጊት መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።

የአሁኑ ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ "ዳግም የአድዋ ድል የመቀዳጀት" ኃላፊነት አለበትም ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊያን በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖና "እኛ የምንላችሁን አድርጉ" የሚል ንግግር በአንዲት ነጻና ሉዓላዊ አገር ቀጥታ ጣልቃ መግባትን እንደሚያንጸባርቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለ27 ዓመት በሥልጣን ላይ የቆየውን ህወሃት መራሹ መንግስት በሕዝባዊ ተቃውሞና መስዋዕትነት ከሥልጣን እንዲለቅ ካደረጉት ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል።

በወቅቱ ወጣቶች "ህገ መንግስቱ እኛን አይወክለንም፤ ኢ ዴሞክራሲ አገዛዝ ለኢትዮጵያ አይመጥናትም" በሚሉ ሃሳቦች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ለለውጥ ወደ ጎዳና ወጥተዋል፤ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሌብነት ተስፋፍቶና የእርስ በርስ ግጭቶች ተበራክተው ሲመጡ የለውጡ ፍላጎት እያየለና ትግሉ እየጋለ መጣ። በህዝብ ትግል ለውጥ እውን ሆነ።

የለውጡ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍተው የነበሩትን ሥር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ወደ ተሻለ ጎዳና እንዲያሻግራት ሃላፊነት እንደጣለበት ሕዝብ አደባበይ በመውጣት አረጋገጠ።

የለውጡ መንግስት በአገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን በአገር በቀል ጥበብ ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወሳል።

ከዚህም አልፎ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነትን ዳግም መመለስና የታላቅ ህዳሴ ግድቡን ወደ  ፍጻሚ በመውሰድ ረገድ ጉልህ ስራ ሲከናወን መቆየቱ አይዘነጋም።

ይህም ኢትዮጵያን በቀጣናው ታላቅና ተጽእኖ ፈጣሪ አገር እያደረጋት የመጣ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭ አገሮች የተጽዕኖ መልኩን እየቀያየረ በመከሰት ኢትዮጵያን እየፈተናት ይገኛል።

በፌዴራል መንግስት ያለውን ሃላፊነት በመተው ወደ ትግራይ የሄደውና በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪነት የተፈረጀው የህወሃት ኮር መሪነት በሰሜን እዝ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም አገሪቷ ተገዳ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ እንድትገባ መደረጉ ይታወቃል።።

በወቅቱም መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ከወሰደና ኢትዮጵያ ከተደቀነባት አደጋ ስትወጣ ምዕራባዊያን በተለያዩ መንገዶች ተጽእኖ ማድረግ መጀመራቸው ተስተውሏል።

ምሁራን እንደሚናገሩት፤ ከዚህ ጊዜ በኋላ በተለይ የአሜሪካን መንግስት "ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ድንበሮቿን መለወጥ አትችልም" በማለት የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህንና ሕግጋትን የጣሰ አቋም እያራመዱ ይገኛል።

የአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ህዳር 05 ቀን 2020 ባወጣው መግለጫ "ኢትዮጵያ ህገ መንግስቷን፣ የውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኗንና የውጭ ድንበሯን መለወጥ አትችልም" ሲል አትቷል።

በተመሳሳይ በቅርቡ በተካሄደው በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በመንግስታቱ ድርጅት አሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ "ኢትዮጵያ ህገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ የውስጥም ሆነ የውጭ ድንበሯን ፈጽሞ መለወጥ አትችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሁለት ቀናት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ይህኑኑ ሃሳብ ደግመዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንደሚሉት፤ መግለጫዎቹ  ኢትዮጵያን "እንደ ጓሮ አትክልት ስንፈልግ እንተክላታላን ሳንፈልግ ደግሞ እንነቅላታለን" የሚል እሳቤ ያላቸው መሆኑን ያንጸባረቃል።

በአፍሪካ ቀንድ በጥንካሬዋ አርአያ እየሆነች የመጣችውን ኢትዮጵያን የማንበርከክ ዓላማን ያነገቡ መሆናቸውን በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የጠቀሱት።

የፍስፍና ምሁሩ ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው መግለጫዎቹ፤ "ለምንድን ነው ምዕራባውያን ስለኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አጥብቀው የተጨነቁት?" የሚል ጥያቄ እንደሚያጭሩ ያመለክታሉ።

የመግለጫዎቹ ሁኔታ አንድ ከእጅ ሊያመልጥ ያለን አገር የማሳደድ አንድምት እንዳለውም አብራርተዋል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በክልሎችም ሆነ በዞንና ወረዳዎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን "ከዚህ እስከ እዚህ ነው"  በሚል የሚያስቀምጠው ነገር እንደሌሌም ነው ዶክተር ብርሃነመስቀል ይናገራሉ።

አስተዳደራዊ ወሰን መንግስታዊ አሰራርንን ተደራሽ ለማድረግ አንዴ የሚሰፋ አንዴ የሚጠብ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንጂ የትኛውንም የዓለም አቀፍ ተቋም የሚመለከት እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ምዕራባውያን በእውነታ ላይ የተመሰረተ አቋም ቢኖራቸው ኖሮ ከኢትዮጵያ የውስጥ አስተዳደራዊ ወሰን ይልቅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሳ የገባችውን ሱዳን ይወቅሱ ነበር። "ይህንንም ሲያደርጉ አይታዩም" በማለት ሞጋች ሀሳብ ያቀርባሉ።

ምእራባውያን ለሰብዓዊ መብት የሚጨነቁ ከሆነ የአሸባሪው ህወሃት በማይካድራ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ በጦር ወንጀል ያስጠይቀው እንደነበር ነው የተናገሩት።  

ነገር ግን ይህንን ያደረገ ወይም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቶ የሰራ የምእራባውያን አገር እንደሌለ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን መንቃት እንዳለባቸው ምሁራኑ ይናገራሉ።

ጩኸቶቹ ሁሉ አንድምታቸው ሌላ መሆኑን በማብራራት።

ምእራባውያን ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን ላይ "ስለ ሰብዓዊ መብት ያገባናል፤ ያስጨንቀናል" በሚል ገብተው ለብተና እንደዳረጓቸውም አውስተው፤ የአሁኑ ዘመቻንም ከዚህ አኳያ ያለውን አንድምታ ኢትዮጵያዊያን በመመርመር አንድነታቸውን አጥብቀው ሊገኙ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የእነዚህ አገር ዜጎች መከራ በገጠማቸው ጊዜም ምእራባውያኑ ፊታቸው ከማዞር ባሻገር እነሱን ለማገዝና ችግሩን ለመፍታት ያደረጉት እዚህ ግባ የሚባል ስራ እንደሌለም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ከጣልያን ፋሽስት ወረራ በላይ አንድ ሆነው አገራቸውን የሚታደጉበት ጊዜ  አሁን መሆኑንም አብራርተዋል።

አባቶቻችን አደዋ ላይ ወራሪ ኃይልን በጦር ጎራዴ እንዳስወደጉት ሁሉ፤ የአሁኑ ትውልድም አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ሀገርን በመታደግ እንዲሁም የአባይ ግድብን በመሙላት "የዳግም አደዋ ድል ኃላፊነት አለበት" ነው ያሉት።  

መንግስትም በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ስራ መስራት እንዳለበትም ምሁራኑ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም