በምርት ዘመኑ 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በምርት ዘመኑ 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ክረምት በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የጥምር ደን ችግኝ የሚተከል መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በአግባቡ ተከናውኖ ወደ ህዳሴ ግድብ የሚገባውን ደለል መከላከል ከተቻለ የአገልግሎት ዕድሜውን 375 ዓመታት ማድረስ እንደሚቻልም ይታመናል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለ140 ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይገመታል።
በመሆኑም የግድቡን የአገልገሎት እድሜ ለማራዘም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ወሳኝ በመሆኑ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ችግኝ መትከል እንደሚገባ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በ2030 ዘላቂ የልማት ግብ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል።
በአራት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም 20 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የልማት ግብ ዕቅዱን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ ገልጸዋል።
በዘንድሮ የሶስተኛው የአረንጓዴ ልማት መረሃ ግብር ከሰባት ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ ተከላው እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላዩን በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚተከሉ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በአባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሰራዎችን በማጠናከር የታላቁ የህዳሴ ግድብን ከደለል መከላከልና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ሳኒ አብራርተዋል።
የአባይ ተፋሰስ ልማት ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤና ደቡብን ጨምሮ፣ በአማራ ክልል 90 ወረዳዎችን፣ በኦሮሚያ 96 እንዲሁም በትግራይም በርካታ አካባቢዎችን የሚሸፍን መሆኑን አስገንዝበዋል።
በእነዚህ አብዛኛው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ መጀመሩን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ዋናው ወደ ግድቡ የሚገባውን ውሃ ማጣራትና ውሃ የመያዝ አቅሙን የሚጎዱን ነገሮችን መከላከል መሆኑን አስረድተዋል።
አባይ የኢትዮጵያዊያን የህልውና መሰረት በመሆኑ በዲፕሎማሲው መስክ እየተደረገ ያለው ትግል እንዳለ ሆኖ የግድቡንም ህልውና መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወደ ህዳሴ ግድብ የሚገባውን ደለል 50 በመቶ መቀነስ ከተቻለ ግድቡ 140 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ይገመታል።
75 በመቶ የሚሆነውን ደለል መከላከል ከተቻለ ደግሞ 246 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚኖረው ይታመናል።
አካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአገራችን አልፎ ለዓለምና ለአህጉሩ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይ የውሃ ሃብትን ለማሳደግ፣ ለሃይል ማመንጫ፣ ለብዘሃ ህይወት ጥበቃና ለደን ልማት እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም የአረንጓዴ ልማቱ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ለአካባቢ ጥበቃም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጎረቤት አገራት የተዘጋጁት ችግኞች ለቀጠናዊ ትብብር፣ ለጋራ ልማትና ትብብር ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።